የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ጉዳይ የአፍሪካ ቀዳሚ አጀንዳ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

105

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 16 ቀን 2015 የአፍሪካን መፃኢ እድል ብሩህ ለማድረግ እና የተሻለች አፍሪካን ለመፍጠር የአፍሪካ መሪዎች የወጣቶችን ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ መስራት እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

አቶ ደመቀ በኒጀር ኒያሚ ከተማ እየተካሄደ ከሚገኘው የአፍሪካ ህብረት መደበኛ ጉባዔ ጎን ለጎን የአፍሪካ ኤሌክትሮኒክስ ግብይት መድረክ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉ ሲሆን የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ጉዳይ የአህጉሪቷ ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

አክለውም የኤሌክትሮኒክስ ግብይት እና ሌሎችም መሰል ውጥኖች በአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ሊደገፉ እንደሚገባ የጠቀሱ ሲሆን ከዚህ አልፎም ግብይቱ የምርጥ ተሞክሮ ማሳያ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

አፍሪካ በዓለም አቀፉ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ፍትሃዊ ድርሻዋን ማግኘት አለባት ያሉት አቶ ደመቀ ይህ ካልሆነ ግን የአፍሪካ ህዝቦች ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ነፃነት ሊያገኙ አይችሉም ብለዋል።

የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካ ለመፍታት እና አፍሪካውያን ጥበብን ለማሳደግና ለመጠበቅ ተመሳሳይ የዲጂታል ተሞክሮዎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድ እና ልማት ጉባኤ እ.አ.አ. በ2021 ባወጣው ሪፖርት መሠረት ዓለም አቀፍ የኢ-ኮሜርስ የግብይት ዋጋ መጠን 26 ነጥብ3 ትሪሊዮን ዶላር የነበር ሲሆን ከዚህም ውስጥ የአፍሪካ ድርሻ አንድ በመቶ ብቻ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም