የአፋር ክልል ሕዝብና መንግሥት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት የድርሻቸውን ይወጣሉ-የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ

139

ሠመራ (ኢዜአ) ህዳር 16/2015 የአፋር ክልል ሕዝብና መንግሥት በፌዴራል መንግሥትና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ገቢራዊነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ አስታወቁ።

በፌዴራል መንግሥትና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ በተካሄደው የሰላም ውይይት ላይ ለተሳተፉ የቡድን  አባላት የአፋር ክልል መንግሥት ያዘጋጀው የምስጋና እና ዕውቅና መርሃ ግብር በሰመራ ከተማ ትናንት ማምሻውን ተካሂዷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በሥነሥርዓቱ ላይ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን  ገልጸዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ያለ ሰላም ዕድገትም ሆነ ልማት የማይታሰብ መሆኑን በፅኑ የሚያምነው መንግሥት ዘላቂ ሰላም  ለማስፈን ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉንም ተናግረዋል።

በዚህ እልህ አስጨራሽ ጥረቱ በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደዉ የሰላም ውይይት ኢትዮጵያን  አሸናፊ ያደረገ የሰላም ስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል።

በፌዴራል መንግሥትና በህወሓት መካከል ለተደረሰው ስምምነትም በሰላም ውይይቱ የተሳተፈው ቡድን አባላት ውይይቱን ብስለት፣ ማስተዋልና ጥበብ በተሞላበት አግባብ በማካሄዳቸው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን አኩርተዋል ብለዋል።

በሰላም ውይይቱ ለተሳተፉት የቡድኑ አባላት በአፋር ክልል ሕዝብና መንግሥት ስም ምስጋና አቅርበዋል።

May be an image of 3 people and people standing

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ባለፉት ሁለት ዓመታት ባጋጠመው ችግር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተጎጂ መሆኑን ገልጸው፤  በተደረሰው የሰላም ስምምነት የአፋር ህዝብና መንግሥት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በሁለቱም ወገኖች ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት የአፋር ክልል ሕዝብና መንግሥት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ አረጋግጠዋል።

የሀገራችንን ሰላምና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ኢትዮጵያዊያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ያሳየነውን አንድነት፣ ህብረትና ትብብር አጠናክረን በልማት መስኩም በመድገም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በንቃት እንረባረብ ሲሉም ጠይቀዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንደገለጹት ከሁለት ዓመት በላይ በወሰደው ጦርነት እንደ ሀገርና ህዝብ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

አምባሳደር ሬድዋን አክለውም በዚህም የኢትዮጵያን ውድቀት ለሚሹ አካሎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን አስከፊ ሁኔታ በመቀልበስ  የሀገሩን ሕልውና እና አንድነት ለማረጋገጥ በከፈለው መስዋዕትነት የሰላም ስምምነቱ እውን መሆኑን ተናግረዋል።


በፌዴራል መንግሥትና በህወሓት መካከል  በተደረሰው የሰላም ስምምነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ  አትራፊ መሆኑን አምባሳደር ሬድዋን በአጽንኦት ገልጸዋል።


በመሆኑም የሰላም ስምምነቱ ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም የሰላም እጦቱ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ የሆነው ህብረተሰብ ለተግባራዊነቱ የመሪነት ሚናውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመርሃ ግብሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ አመራሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም