ቤልጂየም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደምትፈልግ የሀገሪቱ ንጉስ ገለፁ

919

አዲስ አበባ መስከረም 17/2011 ቤልጂየም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የትብብር ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግ የአገሪቱ ንጉስ ገለፁ።

ንጉስ ፊሊፕ ይህንን የገለፁት በቤልጂየም የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ግሩም አባይን የሹመት ደብዳቤ በተቀበሉበት ወቅት ነው።

በዚሁ ወቅት የቤልጂየም ኩባንያዎች መዋእለ ንዋያቸውን በኢትዮጵያ በማፍሰስ በአገሪቱ የምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፉ አገራቸው አንደምትሰራ ንጉሱ መግለፃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።

ቤልጂየማዊያን ኩባንያዎች በኢንቨስትመንት፣ በትምህርትና በቱሪዝም ዘርፎች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰማሩም ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ሂደት በተለይም ደግሞ አገሪቱ ከኤርትራ ጋር ያወረደችው እርቀ ሰላም ያስደሰታቸው መሆኑንም ንጉሰ ፊሊፕ ተናግረዋል።

አምባሳደር ግሩም በበኩላቸው በወቅታዊው የኢትዮጵያና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ በተለይም በለውጡ የተገኙ መልካም ውጤቶች ላይ ለንጉሱ ገለጻ አድርገውላቸዋል።

አምባሳደር ግሩም በቅርቡ ወደ ቤልጂየም ከመዘዋወራቸው በፊት በሩሲያ ተሹመው ይሰሩ የነበሩ አንጋፋ ዲፕሎማት ናቸው።

የኢትዮጵያና የቤልጂየም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው በ1906 ነው።