ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር ተወያዩ

166

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 2015 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር በኒጀር ርዕሰ መዲና ኒያሚ መወያየታቸው ተገለጸ።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የሚመራው የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን ''የአፍሪካ የኢንዱስትሪ ልማት ለአካታችና ዘላቂ የኢንደስትሪ ዕድገትና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ማስፋት'' በሚል ርዕስ በኒያሚ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ሕብረት ልዩ ስብሰባ እየተሳተፈ ነው።

ከስብሰባው ጎን ለጎን አቶ ደመቀ ከሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ጋር ባደረጉት ውይይት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሐት መካከል በተፈረመው የሰላም ስምምነት የአፍሪካ ሕብረት ሚና ወሳኝ እንደነበር ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ በሰሜን ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በሰላም እንዲቋጭና በኋላ ላይም በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ በተደረጉ ስምምነቶች የአፍሪካ ሕብረት ላሳየው በመርህ ላይ የተመሠረተ አቋም ምስጋና ችረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃመት በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ኢንሼቲቭ ላይ ላሳየው የጸና እምነት አድንቀዋል።

ሊቀመንበሩ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፍሪካዊያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም