ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ ጋር ተወያዩ

103

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 15 ቀን 2015 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ፔድሮ ጋር በኒጀር ኒያመሚ ተገናኝተው ተወያዩ።

ውይይታቸውን ያደረጉትም በኒጀር ኒያሚ እየተካሄደ ከሚገኘው ከአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ልዩ መደበኛ ስብሰባ ጎን ለጎን መሆኑም ተገልጿል።

በውይይታቸውም ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊው የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በአዲስ አበባ የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በትብብር እንደሚያዘጋጁ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸውላቸዋል።

ዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤው ከህዳር 19 እስከ ህዳር 23 2015 ዓም በአዲስ አበባ እንደሚዘጋጅ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ኮሚሽኑ በትብብር ለመስራት ያሳየውን ተነሳሽነት አድንቀዋል።

ጉባኤው ኢትዮጵያ በዲጂታላይዜሽን ዘርፉ እያከናወነች ያለውን ስራ በተሞክሮነት ለማሳየት መልካም ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊው መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም