ኢትዮጵያ በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የነቃ ተሳትፎ እያደረገች ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

117
አዲስ አበባ መስከረም 17/2011 ኢትዮጵያ በአሜሪካ ኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረገች  መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ጠቅላላ ጉባዔው የተመድ አባል አገራት በየዓመቱ ለሶስት ወራት ያክል የባለብዙ ወገን (Multilateral) የዲፕሎማሲ ስራቸውን የሚያከናውኑት በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመሆኑ ኩነቱ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል። ጉባኤው የአገራት መሪዎችን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችንና ከፍተኛ ባለስልጣናትን በአንድ ጊዜ በአንድ ቦታ ለማግኘት እድል የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም ዋነኛ ትኩረት ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ በዚህ ወሳኝ መድረክ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንዲቻላት በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ እና ኒውዮርክ በሚገኘው ቋሚ መልዕክተኛዋ በኩል በቂ ዝግጅት ማድረጓን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤቱ ለኢዜአ ገልጿል። የድርጅቱ መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የተመራ ከፍተኛ የመንግስት የልኩካን ቡድኗን በ73ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲሳተፍ ሰሞኑን ወደ ኒውዮርክ ልካለች። ዶክተር ወርቅነህ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለጠቅላላ ጉባኤው ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በዚህም አንኳር አገራዊ እንቅስቃሴዎችን ጨምሮ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን ያነሳሉ ተብሏል።የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ  እና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሳደር ቲቦር ፒተር ናጊ ጋር እዚያው ኒው ዮርክ ተገናኝተው በጋራና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም