በአፋር ክልል የብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን በሚያጠናክር አግባብ እንደሚከበር ተገለጸ

109

ሠመራ፤ ህዳር 13 ቀን 2015(ኢዜአ) በአፋር ክልል 17ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የቆየውን የህዝቦች ወንድማማችነትና ህብረ-ብሄራዊ አንድነትን በሚያጠናክር አግባብ እንደሚከበር የክልሉ ምክር ቤት ገለጸ።

የክልሉ  ወጣቶችና ስፖርት እንዲሁም ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ሰራተኞችና አመራሮች የብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ቀን ዛሬ በሠመራ ከተማ  በፖናል ውይይት አክብረዋል።

በሥነ- ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባኤዋ መይረም አሃው  ፤ ኢትዮጵያ  የተለያዩ ባህልና ቋንቋን ጨምሮ ብዝሃነትን  የሚስተናገድባት ህብረ ብሄራዊት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

ብዝሃነቱ ተፈጥሮ የሰጠችን ውድ ጸጋ መሆኑን  አውቀን በመቀበል በብሔር ብሔረሰቦች  መካከል መከባበርና ወንድማማችነትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በዚህ ውስጥ የሚገኙ   ሀገር በቀል እውቀቶችና መልካም እሴቶችን ለሀገራዊ ልማት በመጠቀም   እጅ ለእጅ ተያይዞ  የብልጽግናን ጉዞ  ማፋጠን እንደሚገባም አሳስበዋል።

በዓሉ በክልሉ እስከ ህዳር 20 ቀን  2015 ዓ.ም ድረስ በየደረጃው  በተለያዩ መርሃ-ግብሮች  እንደሚከበር ገልጸዋል።

 ይህም እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ በክልሉ የሚገኙ ዜጎች እርስ በራሳቸው ተከባብረውና ተቻችለው አብሮ የመኖር የቆየ አኩሪ እሴታቸውን በሚያጠናክር አግባብ  ይሆናል ብለዋል።

በተለይም አንድነትና አብሮነትን በሚያጠናክር የስፖርት ውድድሮች፣ በጽዳት ዘመቻ፣ በደም ልገሳና በሌሎቸም የበጎ አድራጎት ስራዎች በየደረጃው  እንዲከበር አቅጣጫ መቀመጡን ምክትል አፈ - ጉባኤዋ አስታውቀዋል።

በተጨማሪም ህዝባዊ የውይይት መድረኮች በቀጣዩቹ ቀናቶች እንደሚካሄዱም አመላክተዋል።

ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ዘሃራ መሀመድ በሰጡት አስተያየት፤ የብሔሮች ፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ቀን  መከበሩ  ሁሉም ኢትዮጵያዊ ባህሉንና ቋንቋውን ጠብቆ ለማቆየት ብሎም እርስ በርስ በመተዋወቅ ወንድማማችነትን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ዘይኑ መሀመድ ፤ በዓሉ በህዝቦች መካከል የባህልና ቋንቋ ትውውቅን ለማጎልበት እንዲሁም ህብረ-ብሄራዊ አንድነት ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

17ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ቀን  በዓል  በሀገር አቀፍ ደረጃ  ህዳር 29 በሀዋሳ ከተማ እንደሚከበር ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም