ለሀገራዊ እድገቱ ዕቅድ ስኬት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማጠናከር ይገባል–የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን

279

ጂንካ (ኢዜአ) ህዳር 13/ 2015 በኢትዮጵያ ዘንድሮ የ7 ነጥብ 5 ሀገራዊ እድገት ለማስመዝገብ የተያዘው ዕቅድ እንዲሳካ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ሲሉ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ገለጹ።

ምሁራኑ በ2014 በጀት ዓመት የተመዘገበው ሀገራዊ እድገት ለችግሮች የማይበገር ጠንካራ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ እየተገነባ መሆኑን ያመላክታል ሲሉም ተናግረዋል።    

በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ቡሎ ፈይሳ እንዳሉት፣ የተመዘገበው ዕድገት መንግስት የተገበረው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ውጤታማነቱን የሚያሳይ ነው።

በተለይ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት እድገቱ መመዝገቡን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የፓርላማ ገለጻ መረዳታቸውን አስታውሰዋል።  

“አምና በችግር ውስጥ የተመዘገበው የ6 ነጥብ 4 በመቶ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት በፈተናዎች ያልተበገረ ጠንካራ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ እየተገነባ ስለመሆኑ አመላካች ነው” ብለዋል።

ዘንድሮ ለማሳካት የታቀደው የ7 ነጥብ 5 ዕድገት ዕውን እንዲሆን የተጀመሩ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ማጠናከር እንደሚገባም ተመራማሪው አመልክተዋል።

ግብርናውን ለማዘመንና በአዲስ ዕይታዎች ለማጠናከር በተለይ የመስኖ ስንዴን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች መጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

መምህሩ እንዳሉት በአገልግሎት ዘርፍ የተወሰዱ የማሻሻያ ሥራዎች እየተመዘገበ ላለው ሀገራዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ በመሆናቸው ሊጎለብቱ ይገባል።

ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገቱ ቀጣይነት በግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በስፋት መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

ሌላኛው በጂንካ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ እስራኤል በረከት በበኩላቸው “ጦርነት፣ ድርቅ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝና መሰል ችግሮች በነበሩበት 6 ነጥብ 4 በመቶ እድገት መመዝገቡ ተስፋ ሰጪ ነው” ብለዋል።

መንግስት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ቀርጾ  በመተግበር ያሳየው ቁርጠኝነት ለተመዘገበው ዕድገት ድርሻው የላቀ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዘንድሮ ለማስመዝገብ በዕቅድ የተቀመጠውን ውጥን ለማሳካት ሁሉም በተሰማራበት ዘርፍ የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን፣ በቂ የሰው ኃይል እና የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በማቀናጀት የግብርና ምርታማነትን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚገባም ተመራማሪው አመላክተዋል።

እንደ ተመራማሪው ገለጻ በግብርናው ዘርፍ በአዲስ እሳቤ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚኖራቸው አስተዋጽኦ የላቀ ነው።

ምርታማነትን ለማሳደግ በዘርፉ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ማድረግ፤ ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን ማልማትና ሌሎች ተግባራትን ማከናወን ይገባል ሲሉም መክረዋል።

“የሀገር ውስጥ አምራቾችንና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አቅም ማጎልበት፣ የወጪ ንግድን ማበረታታት፣ የተቀባይ ሀገራትን ፍላጎትን መለየትና የብድር አቅርቦትን ማሻሻል ኢኮኖሚውን ያሳድጋሉ” ብለዋል።

በኢኮኖሚ ተዋንያኖች መካከል ትብብርን ማጠናከር፣ ተቋማዊ እድገትን ማበረታታትና ሊደረስ ከታሰበው የልማት ደረጃ ጋር የሚጣጣም የወጪ ምርት ፖሊሲ አስፈላጊ መሆኑንም ተመራማሪው ጠቁመዋል።

የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የገንዘብ አቅርቦት መከታተል እና ጠንካራ የንግድ ቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ በሀገሪቱ አምና 6 ነጥብ 4 በመቶ እድገት እንደተመዘገበ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።