ጣና ሐይቅ የትራንስፖርት ድርጅት እና የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ውህደት ፈጸሙ

172

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 13/2015-- የጣና ሐይቅ ትራንስፖርት ድርጅትን ለማዘመንና ተደራሽነቱን ለማስፋት ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ጋር የውህደት መረሃ-ግብር ተከናወነ።

በውህደቱ መሰረት "ኢትዮ ፌሪስ ጣና"(Ethio Ferries Tana) የተባለ አዲስ ስያሜ ያለው ካምፓኒ እንደሚቋቋም የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት አስታውቋል።

ውህደቱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ የክልሉና የፌዴራል መንግስት የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተከናውኗል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በውህደት መረሃ-ግብሩ ላይ እንዳሉት የጣና ሐይቅ ባህር ትራንስፖርት ድርጅት ለበርካታ ዓመታት የባህር ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።

ነገር ግን ዘመናዊ ወደቦችን በመገንባትና አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን በኩል ችግሮች እንዳሉበትና የተገልጋዩን ማህበረሰብ ፍላጎት ሳያረካ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዘመናዊ የትራንስፖርትና የጭነት ጀልባዎችን ገዝቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ያለበት የአቅም ችግር የድርጅቱ አገልግሎት የተሳለጠ እንዳይሆን ማድረጉን ገልጸዋል።

ድርጅቱ ችግሮቹ እንዲፈቱና ዘመናዊ የባህር ላይ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዲችል ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና የሎጅስቲክ አገልግሎት ጋር እንዲዋህድ መደረጉን ገልፀዋል።

ውህደቱ ድርጅቱ በዘመናዊ የትራንስፖርትና የጭነት ጀልባዎች ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችለው ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ በበኩላቸው፣ የውህደት ስምምነቱ የጣና ሐይቅን ትራንስፖርት ቀልጣፋና ዘመናዊ ለማድረግ የጎላ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

በቀጣይ ፍጥነትና ዘመናዊነትን የተላበሱ የትራንስፖርትና የጭነት ጀልባዎች እንደሚገዙ ጠቁመው፣ "በጣና ሐይቅ ዳርቻዎች የሚገኙ ወደቦችን የማዘመን ስራም ይሰራል" ብለዋል።

ዛሬ የተከናወነው ውህደትም ሥራዎችን በተሻለ ቅንጀት ለማከናወን የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ያመለከቱት።

በውህደቱ መሰረት "ኢትዮ-ፌሪስ ጣና" የተባለ አዲስ ስያሜ ያለው ካምፓኒ ይቋቋማል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም