የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት እስከ ሌሊት 6 ሰዓት አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው

299

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 13/2015 የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ከነገ ህዳር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሌሊት 6 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማጠናቀቁ ተገለጸ።

የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ዳይሬክተር ኢንጂነር ውባየሁ ማሞ እንዳሉት ቤተ መጻሕፍቱ ኢትዮጵያን  የሚያኮራ  ታሪክ ሰሪ ትውልድ በንባብ የሚገነባበት ማዕከል ነው ።

በንግግርና ውይይት የሚያምን ትውልድ የሚገነባው አንባቢ ትውልድ ሲፈጠር መሆኑን ጠቅሰው፤ የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት አንባቢ ትውልድን ለማፍራት  ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል።

ቤተ መጻሕፍቱ ከዚህ ቀደም ከጧቱ 2  ሰዓት እስከ 12  ብቻ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር  አውስተው ተጠቃሚዎች የአገልግሎት ሰዓት እንዲራዘም ሲጠይቁ እንደነበርም ጠቁመዋል።

ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባትም አገልግሎት የሚሰጥበት ሰዓት ማሻሻያ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ከነገ ጀምሮ  ከጧቱ 2 ሰዓት እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት ድረስ  ቤተ መጻሕፍቱ ለህዝብ ክፍት እንደሚሆን ነው የተናገሩት።

በተያያዘ ዜና በኬንያ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት የተሰባሰበ መጻህፍት በኬንያ ዲያስፖራና የቆንስላ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አምባሳደር ዶክተር ደስታ ወልደዮሐንስ በኩል ለቤተ- መጽሐፍቱ ተበርክቷል።

በዛሬው እለት የተሰጡት 164 መጻህፍት መሆናቸውንና በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች የተጻፉ መሆናቸውንም አምባሳደሯ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ 500 የሚሆኑ መጻህፍት በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ጄነራል ባጫ ደበሌ የተሰበሰቡ እንዳሉ በመጥቀስ በቅርቡ ለቤተ-መጽሐፍቱ እንደሚደርሱ ነው የገለጹት።

የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ዳይሬክተር ኢንጂነር ውባየሁ ማሞ፤ ለቤተ-መጽሐፍቱ ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መሰል መጻህፍትን በማሰባሰብ ስጦታ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና የሚያምር የኪነ-ህንጻ ጥበብ ሥራ አርፎበት ከ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ወጭ የተገነባ መሆኑ ይታወቃል።