የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለልብና ለሌሎች ቀዶ ህክምና ስራዎች የሚያገለግሉ የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገለት

102

ጎንደር (ኢዜአ) ሕዳር 13/ 2015 አዲስ ካርዲያክ የልብ ህክምና ማእከል 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ለልብና ለሌሎች የቀዶ ህክምና ስራዎች የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በድጋፍ ሰጠ፡፡

የማእከሉ የቦርድ ሊቀ-መንበር ዶክተር ፍቅሩ ማሩ በድጋፍ ርክክቡ ላይ እንዳሉት የህክምና መሳሪያዎቹ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ ለሚያከናውናቸው ለልብና ለሌሎች የቀዶ ህክምና ስራዎች የሚያገለግሉ ናቸው፡፡

ከህክምና መሳሪያዎቹ መካከልም በቀዶ ህክምና ወቅት ታማሚዎች ከፍተኛ የደም ፍሰት እንዳያጋጥማቸው የደም ፍሰት ማቆሚያና መቆጣጠሪያ መሳሪያ እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል፡፡

በአደጋ ወቅት የሚገጥምን የአጥንት ስብራት በቀላሉ ኦፕሬሽን በማድረግ የአጥንት ቀዶ ህክምና ስራ ለማከናወን የሚረዱ የህክምና መሳሪያዎችም እንደሚገኙበት አመልክተዋል፡፡

በተጨማሪም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የልብ ህክምና አገልግሎት ለሚሰጡ ሃኪሞች የስልጠና ወጪ የሚውል የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ የቦርድ ሊቀ-መንበሩ ለዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት አስረክበዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን በበኩላቸው "ድጋፉ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ የሚሰጠውን የቀዶ ህክምና አገልግሎት ለማሳለጥ ከፍተኛ እገዛ አለው" ብለዋል፡፡

"የቀዶ ህክምና መሳሪያዎቹ የመግዣ ገንዘብ እንኳ ቢኖር በገበያ ላይ በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉ ናቸው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ አስፈላጊ በሆነ ሰዓት የተገኙ የህክምና መሳሪያዎች መሆናቸውን ገለጸዋል፡፡

''የቀዶ ህክምና መሳሪያዎቹ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ በቅርቡ ለመጀመር ላሳበው የልብ ቀዶ ህክምና ማእከል አስፈላጊ ናቸው'' ያሉት ደግሞ የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር አሸናፊ ታዘበው ናቸው፡፡

ድጋፉ በስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ለመጣው የቀዶ ህክምና ስራ አጋዥ ከመሆናቸውም በላይ በመሳሪያ እጥረት በታማሚዎች ላይ የሚያጋጥመውን የቀጠሮ መጉላላት የሚቀነስ መሆኑን አመልክተዋል ፡፡

በድጋፍ ርክክብ ስነ-ስርአቱ ላይ የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎችና የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም