በመኸር ወቅት ካለማነው ሰሊጥ ሽያጭ የተሻለ ገቢ አግኝተናል - የመተማ ወረዳ አርሶ አደሮች

255

መተማ ፤ ህዳር 12 ቀን 2015(ኢዜአ) በመኸር ወቅት ካለሙት የሰሊጥ ምርት ሽያጭ የተሻለ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የመተማ ወረዳ አርሶ አደሮች አስታወቁ።

በመኸሩ ወቅት በምዕራብ ጎንደር ከለማው መሬት ውስጥ  የተሰበሰበ  ከ43 ሺህ 400 በላይ የሰሊጥ ግብይት መፈፀሙን  የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያው ገልጿል።

ኢብራሂም ሰዒድ በመተማ ወረዳ የለምለም ተራራ ቀበሌ አርሶ አደር ሲሆኑ፤ ባለፈው የመኸር ወቅት  ካለሙት መሬት 16 ኩንታል የሰሊጥ ምርት ማግኘት እንደቻሉ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል።

ዘንድሮ  ያለው የሰሊጥ ምርት ግብይት ከዚህ ቀደም ከነበረው ገበያ ዋጋ  የተሻለና የድካማቸውን ያህል ውጤታማ እንደሆኑ  አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅትም አንድ ኩንታል ሰሊጥ 9 ሺህ 500 ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የገበያ ዋጋውም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በአንድ ሺህ 600 ብር ጭማሪ እንዳለው አመልክተዋል።

በዚህም ያመረቱትን ሰሊጥ 152 ሺህ ብር በላይ በመሸጥ ከወጭ ቀሪ 120 ሺህ ብር ትርፍ ማግኘት መቻላቸውን አስታውቀዋል።

ሌላኛው በወረዳው የአጋም ውሃ ቀበሌ  አርሶ አደር ከማል ዑስማን በበኩላችው፤  በ3 ሄክታር መሬት ካለሙት ሰሊጥ 11 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ከዝናብ መብዛት ጋር በተያያዘ በምርታማነት ላይ ተፅዕኖ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ ያለው ገበያ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

''ኩንታሉን 9 ሺህ 800 ብር በመሸጥ ወጭዬን ከመሸፈን አልፎ የተሻለ ትርፍ አግኝቻለሁ'' ያሉት አርሶ አደሩ፤ በእርሻ ውል ስምምነቱም የተሻለ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል።

የባለሃብቶች ተወካይ   አቶ መላኩ ትዛዙ እንዳሉት ፤ ከአርሶ አደሩ ጋር ውል በመግባት ሰሊጥ ካለው ወቅታዊ ገበያ ጭማሪ በማድረግ ምርቱን እየተረከቡ ነው።

እስካሁንም "ለሮዝ ስታር ትሬዲንና ጉብማውንት"  የንግድ ድርጅቶች ከ6 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥ መገዛቱን ጠቅሰው፤ የምርት ግዥው መቀጠሉንና  ምርቱም ለውጭ ገበያ የሚቀርብ መሆኑን ተናግረዋል።

በምዕራብ ጎንደር በመኸሩ ወቅት ከለማው መሬት   የተሰበሰበ  ከ43 ሺህ 400 በላይ  ሰሊጥ ለግብይት መቅረቡን  በዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ  የቅባት እህሎች ግብይት ባለሙያ አቶ ጌታቸው ሀይሌ ገልጸዋል።

ግብይት እየተፈፀመ ያለው ሰሊጥም የጥራት ደረጃውን ጠብቆ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ መሆኑን ጠቁመው፤ 

የዘንድሮው  የሰሊጥ ግብይት ስርዓት አርሶ አደሩን ይበልጥ  ተጠቃሚ ማድረጉን አስረድተዋል።

በዞኑ በመኸሩ  ወቅት ከ122ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥ የሰብል ዘር መልማቱና ምርቱም እየተሰበሰበ  መሆኑን  ከዞኑ ግብርና መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በልማቱም  ከ50ሺህ በላይ አርሶአደሮችና 500 የሚጠጉ ባለሃብቶች መሳተፋቸውም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም