ባህልና እሴቶቻችንን ለትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻችንን እንወጣለን- የብሔረሰብ ተወካዮች

153

ደሴ ህዳር 12 ቀን2015 (ኢዜአ) አንድነታችንና ሰላማችን በመጠበቅ ባህልና እሴቶቻችንን ለትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ በአማራ ክልል የሚገኙ የተለያዩ የብሔረሰብ ተወካዮች ገለፁ፡፡

በአማራ ክልል ደረጃ 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓል በከሚሴ ከተማ ትናንት ተከብሯል።

የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ተወካይ ወይዘሮ ሙሉ አዳም እጅጉ የእርቀ ሰላም፣ መተጋገዝ፣ አብሮነት፣ በደቦ መስራት፣ የአመጋገብ ስርዓት፣ ባህላዊ አልባሳትና ውዝዋዜዎች ክልሉ ከሚታወቅባቸው ባህላዊ እሴቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

"የብሄረሰብ መገለጫ የሆኑ ባህሎችና እሴቶችን በእንደዚህ አይነት የጋራ መድረክ ላይ አውጥቶ ማስተዋወቁ የክልሉንም ሆነ የአገሪቱን  ገጽታ ለመገንባት አስተዋጽኦው የላቀ ነው" ብለዋል።

"አንድነታችንና ሰላማችን በመጠበቅ ከአባቶቻችንና ከእናቶቻንን የወረስናቸውን ድንቅ ባህልና እሴቶች ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻችንን እንወጣለን" ሲሉ አስታውቀዋል።

ሌላው የአርጎባ ብሔረሰብ አስተዳደር ልዩ ወረዳ ተወካይ አቶ አብዱ ሸህ መሃመድ በበኩላቸው "የአርጎባ ብሔረሰብ ከአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሞና ሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በመከባበርና በመፈቃቀር ባህልና ወጉን ጠብቆ የሚኖር ነው" ብለዋል፡፡

ብሔረሰቡ ልዩ የባህላዊ ቤት አሰራር፤ አጨዋወት፤ አመጋገብ፣ ግጭት አፈታትና ሌሎች አንድነትንና ሰላምን የሚያጠናክሩ ባህሎች ያሉት መሆኑን አስረድተዋል።

"በየዓመቱ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ ያሉንን ባህሎችና ወጎች በማስተዋወቅ ለአገር ገጽታ ግንባታ ለማዋል ያግዘናል" ብለዋል።

"እንደ ሀገር አኩሪ ባህሎችና እሴቶች በመጤ ባህሎች እንዳይበረዙ በጋራ መስራት ይኖርብናል" ያሉት ደግሞ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ተወካይ ወጣት የሱፍ ሱልጣን ናቸው፡፡

ወጣቶች ከአባቶቻችን የወረስናቸውን ባህልና እሴቶች ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ከግንዛቤ ፈጠራ ጀምሮ በቅንጅት እየሰራን ነው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንም የድርሻቸውን እንደሚወጡ የብሄረሰብ ተወካዮቹ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም