የኢትዮጵያ አንጋፋ ሠዓሊያን የሚሳተፉበት የሥዕል አውደ-ርዕይ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

289

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ህዳር 12/2015 / የኢትዮጵያ አንጋፋ ሠዓሊያን የሚሳተፉበት የሥዕል አውደ-ርዕይ በአዲስ አበባ አብራክ የሥነ-ጥበብ ማዕከል ሊካሄድ ነው።

የሥዕል አውደ-ርዕዩ ከኅዳር 15 እስከ ኅዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም ለ15 ቀናት የሚቆይ ሲሆን ሰባት አንጋፋ ሠዓሊዎች የሚሳተፉበት ነው።

ሠዓሊዎቹም ከ1950ዎቹ መጀመሪያ እስከ 1960ዎቹ መጨረሻ በአለ የሥነ-ጥበብ ዲዛይን ትምህርት ቤት የተመረቁ ቀደምት ተማሪዎችና ከፊሎቹም በትምህርት ቤቱ ላይ በማስተማር ላይ የሚገኙ ናቸው።

የአብራክ የሥነ-ጥበብ ማዕከል የቦርድ አባል ወይዘሮ ዓይናለም እምሩ፤ አውደ-ርዕዩን ማዘጋጀት ያስፈለገው ለኢትዮጵያ ባለውለታ የሆኑ አንጋፋ ሠዓሊዎችንና ሥራዎቻቸውን ለማስተዋወቅ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የሥነ-ጥበብ ማዕከላት የሥዕሎች መሸጫ ቦታዎች ብቻ ሳይሆኑ ለዕይታ የሚቀርቡባቸው እንደሆኑም ግንዛቤ ለመስጠት እንደሆነ ገልፀዋል።

በጊዜ ሂደትም የአብራክ የሥነ-ጥበብ ማዕከልን ወደ ትልቅ ሜጋ የሥነ-ጥበብ ማሳያ በመቀየር የሙዚየም ሚና ያለው ማዕከል ለማድረግ መታሰቡንም ተናግረዋል።

ለሥነ-ጥበብ ሥራ ምቹ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ዓይናለም፤ እንዲህ ዓይነቱ የሥዕል አውደ-ርዕይ በተከታታይ መደረግና መለመድ ያለበት እንደሆነ ገልፀዋል።

በአብራክ የሥነ-ጥበብ ማዕከል ሥራዎቻቸውን ከሚያቀርቡት ሠዓሊያን መካከል አብዱረህማን ሸሪፍ፣ ወርቁ ጎሹ፣ ዘሪሁን የትምጌታ፣ ሎሬት ደስታ ሐጎስ፣ ቱሉ ጉያ፣ ጥበበ ተርፋ እና  ልዑልሰገድ ረታ ይገኙበታል።

በአውደ-ርዕዩም 34 ሥዕሎች ለእይታ እንደሚቀርቡም ተጠቁሟል።

ማዕከሉ አውደ-ርዕዩን ለማዘጋጀት ዘጠኝ ወራት የፈጀበት ሲሆን የሰባቱን ሠዓሊዎች ሥራ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በስፓኒሽ ቋንቋዎች መጽሔት በማዘጋጀት አሳትሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም