በመዲናዋ ያለአገልግሎት ለረዥም ጊዜ ታጥሮ የተቀመጠ 90 ሄክታር መሬት ውል በማቋረጥ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል

221

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 12 ቀን 2015 በአዲስ አበባ ከተማ ያለአገልግሎት ለረዥም ጊዜ ታጥሮ የተቀመጠ 90 ሄክታር መሬት ውል በማቋረጥ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ተቋማትና ግለሰቦች ለረጅም ጊዜ አጥረው ያስቀመጡት 90 ሄክታር መሬት ውላቸው እንዲቋረጥ ማድረጉን የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ቀነዓ ያደታ ተናግረዋል።

ዶክተር ቀነዓ ያደታ እንደተናገሩት፤ በቀጣይ ውላቸው የተቋረጠው መሬት በግልጽ ጨረታ ለአልሚዎች እንደሚተላለፍ ተናግረዋል።

ውላቸው ከተቋረጡ ቦታዎች መካከል አንዳንዶቹ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ያለ ልማት ታጥረው የተቀመጡ ናቸው።

በተጨማሪም ግምባታቸው ተጀምሮ ያልተጠናቀቁ 1 ሺህ 200 ፕሮጀክቶች እስከ ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም እንዲያጠናቅቁ እና ጊዜያቸው ያላለፈ ነገር ግን ግንባታ ያልጀመሩት ደግሞ በፍጥነት ግንባታ እንዲጀምሩ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተናግረዋል።

ያለ ልማት ታጥሮ የተቀመጠው ቦታ መንግስትና የከተተማዋ ነዋሪዎች መጠቀም የነበረባቸውን እንዳይጠቀሙ ማድረጉንም ነው ያነሱት፡፡

ሌብነትና ህገ-ወጥ የመሬት ወራርን ጨምሮ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በተቀናጀ መልኩ ለመፍታት እየተሰራ ስለመሆኑም የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ቀነዓ ያደታ ተናግረዋል።

በዚህም በመዲናዋ ከመሬት አስተዳደር ስርዓት ጋር በተያያዘ 5 ችግሮች ተለይተው መፍትሔ ለመስጠት አቅጣጫ መቀመጡን ነው የገለጹት፡፡

ሌብነትና የመሬት ወራራን መከላከል፣የመሬት አስተዳደር ስራን ማዘመን፣ጠንካራ የፍትህ ስርዓት መዘርጋት ደግሞ ትኩረት ከተሰጠባቸው ስራዎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኀብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የመሬት ወረራን እና ሌብነትን ለመከላከል እንደሚሰራም እንዲሁ፡፡

በአጠቃላይ ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ጊዜያዊና ዘላቂ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተቀምጠው ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ 25 በመቶ የሚሆነው መሬት በካዳስተር ተመዝግቦ መያዙን ገልጾ፤ በቀጣይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መሬትን መዝግቦ ለመያዝ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በተጨማሪም በከተማዋ 161 ሺህ ኮንዶሚኒዬም ቤቶችን በዘመናዊ ካዳስተር መመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል።

የከተማ ነዋሪዎች ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም