ሀይልና ጉልበት መወደድና መፈራት የሚገኘው ከአንድነት ነው-ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

92
አዲስ አበባ መስከረም 16/2011 ''የመስቀል በዓልን ስናከበር ለወዳጅ ብቻ ሳይሆን ለባላጋራም ይቅርታን በማድረግ በፍቅርና በአንድነት ሊሆን ይገባል'' ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ተናገሩ። ''ሀይልና ጉልበት መወደድና መፈራት የሚገኘው ከአንድነት  መሆኑን መገንዘብ'' ይገባልም ብለዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የ2011 ዓ.ም የደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል ። በዚሁ ክብረ በዓል ብጹእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባስተላለፉት መልዕክት እንደተናገሩት፤ መስቀል ለወዳጅ ብቻ ሳይሆን  ለበዳይም ይቅርታ በማድረግ የተጣላው ታርቆ በአንድነት የሚከበር በዓል ነው። የመለያየት፣ ራስን ብቻ የመወድድ፣ የጥላቻና የመጠራጠር ዝንባሌዎችን ማስወገድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የደመራ በዓል ሲከበር የተበታተኑትንና ተራርቀው የነበሩ እንጨቶችን  አንድ ላይ ተሰባስበው የሚዘጋጁት ህዝቡም በተመሳሳይ ተሰባስቦ እንዲያከብር ለማሳየት እንደሆነም ተገልጿል። ህዝቡም ከዚህ በመማር የፍቅር ምሳሌ የሆነውን የመስቀል በዓልን ሲያከብር በአንድነት በመሰባበሰብ ሊሆን እንደሚገባ ብጹዕነታቸው ተናግረዋል። በ2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እየተከበረ በሚገኘው የመስቀል በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርኮች ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እና ብጹአን አባቶች ተገኝተዋል። ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ምዕመናን፣ ከተለያየ አገር የመጡ ቱሪስቶች፣ የተለየዩ ገዳማት አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት ዲያቆናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ታድመውበታል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም