ማዕከሉ የቡና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተሉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝ ገለጸ

166

ሐዋሳ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 የቡና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተሉ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የምርምርና ስርፀት ሥራዎችን በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል ገለፀ፡፡

የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል አዋዳ ግብርና ምርምር መለስተኛ ማዕከል በሲዳማ ክልል ይርጋለም ከተማ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ በኩታ ገጠም የሚያለማው የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን ለቡና አምራች አርሶ አደሮችና ለባለድርሻ አካላት አስጎብኝቷል።

የወንዶ ገነት ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ከፍተኛ ተመራማሪ ሙሉቀን ፊሊጶስ የቡና ምርታማነትን ማሳደግ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ቡና ምርትና ምርታማነት አለማደግ ያልተሸሻሉና ያረጁ ቡናዎች በስፋት መገኘታቸው እንዲሁም የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የማሳ እንክብካቤ ውስንነቶች በዋናነት እንደሚጠቀሱ አስረድተው፤ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ማዕከሉ በተለይ በአዋዳ መለስተኛ ማዕከል አማካይነት የተሻሻሉ ዝርያዎችን በምርምር ለማውጣት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረው፤ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ በኩታ ገጠም እየተሰራ ያለው ስራ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ማዕከሉ እስካሁን ቆቲ (85257)፣ አንጋፋ (1377) የተሰኙና ሌሎች አራት በምርምር የተገኙ አዳዲስ ዝርያዎች በሲዳማ እና በደቡብ ክልሎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች በማሳቸው ላይ አስተዋውቋል።

የአዋዳ ግብርና ምርምር መለስተኛ ማዕከል የቡና አያያዝ ተመራማሪ ለታ አጀማ በበኩላቸው አዳዲስ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በሲዳማ ክልል በስምንት ክላስተሮች በ60 ሄክታር ማሳ ላይ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቡና ቴክኖሎጂን ባጠረ ጊዜና በሰፋፊ ክላስሮች ላይ ለማላመድ የቡና ተፈጥሯዊ ባህሪ፣ የቆየው ዘልማዳዊ የአመራረት ዘዴና ሌሎች ምክንያቶች ችግር መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቡና በአጭር ጊዜ ምርት የማይሰጥ ተክል እንደመሆኑ የኢኮኖሚ መሰረቱን በማሳው ላይ ላደረገው አርሶ አደር ያረጁ ቡናዎችን መጎንደልና በአዲስ መተካት ሕይወቱን አስቸጋሪ እንደሚያደርግበት ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ማዕከሉ አዳዲስ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በሚያስተዋውቅበት ወቅት ከቡና ጋር አብረው ሊለሙ የሚችሉ እንደ እንሰት፣ ሙዝ እና ሌሎች በቶሎ የሚደርሱ ሰብሎችን ምርትና ምርታማነትን በሚያሻሽል መልኩ ስብጥር እርሻን የሚያለማበትን ዘዴ ጭምር ማሳየት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በማዕከሉ አማካይነት በይርጋለም ከተማ ለ21 ሆነው በ8 ነጥብ 5 ሄክታር በኩታ ገጠም ማሳ የተሻሻለ የቡና ዝሪያ ቡና እያለሙ ካሉ አርሶ አደሮች መካከል ደምሴ ቡአኔ እና ወጣት ዮሴፍ ጃፓን ያረጁ ቡናዎችን በመንቀል በአዲስ መተካታቸውን ተናግረዋል፡፡

በቁርጠኝነት ወደ ልማቱ በመግባት በችግኞቹ መሀል የአፈር ለምነትን የሚያሻሽሉና በፍጥነት የሚደርሱ ሰብሎችን በስብጥር በመትከል ኑሯቸውን መደጎማቸውና አሁን ላይ ጥሩ ውጤት ለማየት መብቃታቸውን ገልፀዋል፡፡

አዲስ የተከሉት የተሻሻለ ዝርያ ቡና በሁለት ዓመት ውስጥ የተሻለ ምርት እንደሰጣቸውም ነው የተናገሩት፡፡

ጥሩ ምርት ለማግኘት ተገቢውን እንክብካቤ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ከፍግ፣ ቆሻሻና የተለያዩ ዕጽዋቶች የተፈጥሮ ማዳበሪያ ከማዘጋጀት ጀምሮ ለማሳቸው ከወትሮው የተለየ ክትትል እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

የይርጋለም ከተማ ሁሉም የገጠር ቀበሌያት ስፕሻሊቲ ቡናን በማምረት የሚታወቁ መሆናቸውም በመርሀ ግብሩ ላይ ተጠቁሟል፡፡

በመስክ ምልከታው ላይ የወንዶ ገነት እንዲሁም የጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ ከሲዳማ ክልልና ከይርጋለም ከተማ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም