የኢትዮጵያን ክብርና ፍላጎት ከመቼውም ጊዜ በላይ የማስጠበቅ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

174

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 ዲፕሎማቶች የኢትዮጵያን ክብርና ብሔራዊ ፍላጎት ከመቼውም ጊዜ በላይ የማስጠበቅ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መሆናቸውን አውቀው በከፍተኛ ኃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

ዲፕሎማሲ በዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታ ውስጥ ቀን ከሌት ያለ ዕረፍት መስራትን የሚጠይቅ በመሆኑ ዲፕሎማቶች ራሳቸውን በሁሉም መስክ ማብቃትና በንቃት መስራት እንዳለባቸውም ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዋና መስሪያ ቤትና በተለያዩ ሀገራት ኢትዮጵያን ወክለው ለሚሰሩ ዲፕሎማቶች በአፍሪካ የአመራር ልህቀት አካዳሚ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።

ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በመድረኩ በመገኘት ልምዳቸውን አካፍለዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የለውጥ ሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ ብቁና የዓለምን ተለዋዋጭ ሁኔታ የሚረዱ ዲፕሎማቶችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የዓለም ጂኦ-ፖለቲካ በፍጥነት እየተለዋወጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዲፕሎማቶች በዚህ አውድ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅምን እና የሀገር ክብርን ባስቀደመ መልኩ በኃላፊነት መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ደመቀ አክለውም ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር፣ ወዳጅነቷን ለማደስ፣ ከአፍሪካውያን ጋር አህጉራዊ አንድነትን ለማጠናከር የተለያዩ መርሃ ግብሮች መጀመሯን አንስተዋል።

በዓለም አቀፍ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ውስጥ ጠንካራ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ላተኮረ ወዳጅነት ትኩረት ሰጥታለች ነው ያለት።

በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ውስጥ ኢትዮጵያ በቂ ውክልና እንዲኖራትና ተቋማቱ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ እየሰራን ነው ብለዋል።

ከየሀገራቱ ጋር ያላትን ግንኙነት በማጤን ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ለመፍጠር በመንቀሳቀስ ላይ መሆኗንም አክለዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት አቋምና አካሄድ የሚመለከተው አዲሱ ፖሊሲ ለመጽደቅ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ነው ብለዋል።

ዲፕሎማቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ክብር የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት ምዕራፍ ላይ መሆናቸውን ሊገነዘቡ ይገባል ነው ያሉት።

የተመደቡበትን ሀገር ባህል እና ቋንቋ በአግባቡ በማወቅም የኢትዮጵያን ጥቅም፣ ታሪክና ገፅታ በማጉላት አሻራቸውን ሊያሳርፉ እንደሚገባም እንዲሁ።

ተለዋዋጭ በሆነው የዓለም ፖለቲካ የአገርን ጥቅም አስጠብቆ ለመዝለቅ ዲፕሎማቶች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት የሚያጠናክሩ የሪፎርም ስራዎች እያካሄደ ነው ብለዋል።

የዲፕሎማት ስራ ሁልጊዜ መማርን፣ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን መረዳትንና የመተንተን አቅምን ይፈልጋል ያሉት አቶ ደመቀ፤ ዲፕሎማቶችም ራሳቸውን ብቁ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዲፐሎማቶቹን አቅም ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የስልጠና መድረኩም የዚሁ አካል ነው ብለዋል፡፡

አሁን የተጀመረው የስልጠና መድረክም ልምድን በማካፈል የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ስራ ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር እንደሚያግዝ አንስተዋል፡፡

በተጨማሪ ነባርና ጀማሪ ዲፕሎማቶች የሚገናኙበት የዲፕሎማት ክለብ እንደሚቋቋም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም