ታላቁ ሩጫ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ፋይዳ አለው-የውድድሩ ተሳታፊ ውጭ አገራት ዜጐች

302

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታና እሴቶች ለዓለም ለማስተዋወቅና ለገፅታ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ያለው ውድድር መሆኑን በ22ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ከተለያዩ ሀገራተ የመጡ ዜጎች ገለፁ፡፡

ለ22ኛ ጊዜ ዛሬ በአዲስ አበባ የተካሄደው የ'ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ' የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ውድድር የተለያዩ አገራት ታዋቂ አትሌቶችን እና የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ ከ40 ሺህ በላይ ህዝብ አሳትፏል።

የውድደሩ ተሳታፊ የውጭ አገር ዜጎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የታላቁ ሩጫ ውድድር ከተሳታፊው ህዝብ ብዛት ጋር ተዳምሮ ልዩ ድምቀት እና ውበት ያለው ውድድር እንደሆነ ተናግረዋል።

ታላቁ ሩጫን ለሁለተኛ ጊዜ የተሳተፈው በኢትዮጵያ የስዊዲን ኤምባሲ ባልደረባ የሆነው ክርስቲያን ታላቁ ሩጫ የኢትዮጵያ ታላቅነት እና የህዝቧን እንግዳ ተቀባይነት ያረጋገጠ ትዕይንት እንደሆነ ገልጿል።

የዓለማችን ታላላቅ አትሌቶችን ባበረከተችው ኢትዮጵያ በ10 ሺዎች ከሚቆጠር ህዝብ ጋር ሩጫውን በመሳተፉም ትልቅ ደስታ እንደፈጠረበት ነው የተናገረው።

አትሌቲክስ ለሰው ልጅ ጤና ከሚያስገኘው ጠቀሜታ አኳያ ሁሉም ሊያዘወትረው እንደሚገባ ገልጾ፤ በቀጣይም በውድድሩ መሳተፉን እንደሚቀጥል አረጋገጧል።

ከአየርላንድ የመጣችው አያን ታያን በበኩሏ ሩጫ የኢትዮጵያውያን ባህል እንደሆነ ጠቅሳ፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ ሰዎች ከንጋት ጀምሮ ሲሮጡና አካላዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መመልከቷን አንስታለች።

ታላቁ ሩጫን ለ10ኛ ጊዜ መሳተፏን ገልጻ፤ ውድድሩ የኢትዮጵውያንን አንድነት ከማጠናከር ባሻገር ኢትዮጵያን ለተቀረው ዓለም ለማስተዋወቅና ገጽታዋን ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግራለች።

ውድድሩ የውጭ አገራት ዜጎችን ማሳተፉም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማሳደግ ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው በመጠቆም።

ተሳታፊዎቹ በመላው ዓለም እየታወቀ የመጣው ታላቁ ሩጫ ውድድር ለአትሌቲክስ እና ለሌሎች ስፖርት አይነቶች ዕድገት በጎ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ ውድድሩ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባልም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም