በአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ ለሚሆኑ ታዳጊ አገራት ማካካሻ የሚያደርግ ልዩ ፈንድ ፀደቀ

696

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 የበለጸጉ ሀገራት በሚለቁት ካርበን ምክንያት በሚደርሰው ብክለት ለሚጎዱ ታዳጊ አገራት ማካካሻ የሚያደርግ ልዩ ፈንድ እንዲቋቋም የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባዔ ወሰነ።

በግብፅ ሻርም ኤል-ሼክ ሲካሄድ የሰነበተው የአየር ንብረት ጉባዔ (COP-27) 'ኪሳራ እና ጉዳት' የተሰኘ ልዩ የማካካሻ ፈንድ እንዲቋቋም በማጽደቅ ዛሬ ተጠናቋል።

ልዩ ፈንዱ በበለጸጉ አገራት በጋዝ ልቀት ሳቢያ በሚከሰተው የሙቀት መጨመር በታዳጊ አገራት ላይ የሚያስከትለውን ጉዳትና ኪሳራ የሚሸፍን ነው ተብሏል።

በተሳታፊ አገራት ሌሊቱን ሰፊ ክርክር የተካሄደበት ይኸው ፈንድ በመጨረሻም ታዳጊ አገራት ባቀረቡት ጠንካራ የመከራከሪያ ሃሳብ አጠቃላይ ስምምነት ላይ ተደርሶ ሊጸድቅ ችሏል።

በዚህም የበለጸጉ አገራት በአየር ንብረት ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖና ወጭዎችን ለመሸፈን የሚያስችል የ"ኪሳራ እና ጉዳት" ልዩ ፈንድ መጽደቁን የቲአርቲ ወርልድ ዘገባ አመላክቷል።"

የኪሳራ እና ጉዳት” ልዩ ፈንድ እንዲቋቋም መወሰኑ በአየር ንብረት ቀውስ ምክንያት ህይወታቸው፣ ኑሯቸው እና ባህላቸው ለጉዳት የተዳረገባቸው ማኅበረሰቦችን ለመደገፍ ትልቅ እርምጃ ነው ሲሉ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ አወድሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም