የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ስናከብር ኢትዮጵያዊ አንድነትን፣ ዘላቂ ሰላምንና ብልጽግናን በማጠናከር መሆን ይገባዋል - አፈ ጉባዔው

167

ከሚሴ (ኢዜአ) ህዳር 11 ቀን 2015 ''የብሔር ብሔረሰቦች ቀንን ስናከብር ኢትዮጵያዊ አንድነትን፣ ዘላቂ ሰላምንና ብልጽግናን በማጠናከር መሆን ይገባዋል'' ሲሉ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለፁ።

በአማራ ክልል 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ''ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን ለዘላቂ ሰላማችን'' በሚል መሪ ሐሳብ በከሚሴ ከተማ እየተከበረ ነው።

በመድረኩ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ የየክልሎች ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንደገለጹት 17ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሲከበር አንድነትና ሰላምን፣ ወንድማማችነትንና ብልጽግናን በማጠናከር መሆን አለበት።

"ህብረ ብሔራዊነታችን የማንነታችን መገለጫ ዓርማና ማህተማችን ነው" ያሉት አፈ-ጉባኤው፤ ቀኑ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን በሚያጠናክር መልኩ በፌዴራል ደረጃ በሲዳማ ክልል አዘጋጅነት ህዳር 29 ቀን 2015ዓ.ም ይከበራል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና የግዛት አንድነት በጠበቀ መልኩ መንግስት የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ስምምነት መፈራረሙን የጠቆሙት አፈ ጉባዔው፤ ለተግባራዊነቱም ሁሉም በየደረጃው ማገዝና መተባበር ይጠበቅበታል ብለዋል።

በመሆኑም አለመግባባቶችን በውይይት መፍታትና የአባቶቻችንን ባህልና እሴት ጠብቀን የኢትዮጵያን ሰላምና እድገት የማይፈልጉትን ሁሉ ማሳፈር ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል።

በተለያየ ጊዜ በሚገጥመን መሰናክል መውደቅ ሳይሆን መሰናክሉን በጋራ ማለፍና ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው በክልሉ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ዘላቂ አንድነትንና ሰላምን በሚያጠናክር መልኩ መከበር ጀምሯል ብለዋል።

በተለይም ውስብስብ ፈተናዎችን አልፈን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በጠበቀ መልኩ የሰላም ስምምነት በተደረሰበት ወቅት በዓሉ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ነው ያሉት።

''በዓሉ አንድነታችንንና ሰላማችንን በማስጠበቅ ቱባ ባህልና እሴቶቻችንን ለትውልዱ በማስተላለፍ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ያግዛል'' ያሉት ደግሞ የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን ናቸው።

የአባቶቻችንን ባህልና እሴት በመጠበቅና በመንከባከብ ትውልዱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲጠብቅም እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

የተለያየ ብሔር፣ እምነት፣ ቋንቋና ባህል መኖር አንዱ ለሌላው ውበት፣ ጋሻና መከታ እንጂ ስጋት ሊሆን እንደማይገባ ጠቁመው፤ አንድነታችንን ጠብቀን የብልጽግና ጉዟችንን እናረጋግጣለን ሲሉም ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አስያ ከማል በበኩላቸው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማጠናከር ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የብልጽግና ጉዞ የድርሻችንን እንወጣለን ብለዋል።

በተለያዩ ክልሎች የብሔር ብሔረሰቦች ቀን መከበሩ ደግሞ የእርስ በእርስ ግንኙነታችንን አጠናክረን የበለጠ እንድንሰራ ያግዘናል ብለዋል።

በዝግጅቱ የተለያዩ ክልል ተወካዮች የተገኙ ሲሆን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ባህል፣ ወግና ልማድ የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይም ለእይታ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም