ቢሮው በትምህርት ቤቶች አካባቢ የመማር መስተማር ስራውን በሚያውኩ ከ1ሺህ በላይ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ወሰደ

118

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 9 ቀን 2015 የአዲስ አበባ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በመዲናዋ በትምህርት ቤቶች አካባቢ የመማር መስተማር ስራውን በሚያውኩ ከ1 ሺህ በላይ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡

ቢሮው እርምጃውን የወሰደው በዛሬው እለት በወሰደው ድንገተኛ ኦፕሬሽን መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ጉዳዩን አስመልክተው ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ዛሬ ከቀኑ 8:00 ጀምሮ አዲስ አበባ  ከተማ  በሁሉም ወረዳዎች በተጠና መንገድ በትምህርት ቤቶች ዙሪያ የመማር ማስተማሩን በሚያውኩ ድርጅቶች ላይ  የተለያዩ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ጫት ቤቶችና መጠጥ ቤቶችን ጨምሮ ከ አንድ ሺህ 246 በላይ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት፡፡

እርምጃ የተወሰደባቸው ድርጅቶች ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዳይከታተሉ የሚያደርጉ ከመሆናቸውም በላይ ለሱስ ተገዥ እንደሚያደርጓቸውም ጠቁመዋል፡፡

ፔንሲዮኖችና ህገ-ወጥ ጋራዥ ቤቶችም እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል መሀናቸውን አንስተዋል፡፡

ቢሮው በቀጣይም ጥናትን መሰረት በማድረግ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የኀብረተሰቡን ሰለማዊ ኑሮ በሚያውኩ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም