የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ የመንግስትን ወርሃዊ ኪሳራ ከ10 ቢሊዮን ብር ወደ 4 ቢሊዮን ብር ዝቅ አደረገ

421

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 9 ቀን 2015  የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ የመንግስትን ወርሃዊ ኪሳራ ከ10 ቢሊዮን ወደ 4 ቢሊዮን ብር ዝቅ ማድረጉን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ገለፀ፡፡

ባለፉት ሶስት ወራት በነዳጅ ማደያዎች ላይ በተጣለ ተጨማሪ እሴት ታክስ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንም ነው ባለስልጣኑ ያስታወቀው፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከሶስት ወራት በፊት ተግባራዊ የሆነው የታለመለት ነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ በዘርፉ እምርታ እያመጣ ነው።

ለአብነትም መንግስት በየወሩ በነዳጅ ድጎማ ይደርስበት የነበረውን ኪሳራ ከ10 ቢሊዮን ወደ 4 ቢሊየን ብር መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።

መንግስት እስካሁን በነዳጅ ድጎማ 171 ቢሊዮን ብር ዕዳ ወይም ኪሳራ እንዳለበት ጠቅሰው፤ የድጎማው ሂደቶች እየተስተካከሉ ሲመጡ ቀስ በቀስ ዕዳውን መቀነስ ያስችለዋል ብለዋል።

መንግስት ለነዳጅ ግዥ የሚያወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለመቀነስ እንደ ፖሊሲ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች እንዲገቡ ማበረታቻዎች ተግባራዊ እንደሚደረግም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ቴክኖሎጂን በመጠቀም የነዳጅ ተደራሽነት ላይ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ ጠቅሰዋል።

በዚህም ነዳጅ በሚያመላልሱ አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎችና ነዳጅ ማደያዎች ላይ ቴክኖሎጂዎችን በመግጠም ቁጥጥር ስራውን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ከዓለም የነዳጅ ገበያ ዋጋ አንጻር አሁንም ድጎማ እንደሚያደርግ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ፤ ለአብነትም በዓለም አቀፍ ዋጋ ቢሆን ኖሮ አሁን ላይ ናፍታ 81 ብር፤ ቤንዝን ደግም 66 ብር በሊትር ይሸጥ ነበር ብለዋል።

ከድጎማ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ በታሪፍና መሰል ጉዳዮች ላይ አሁንም በተለይ በክልል ዋና ዋና ከተሞች የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ባለስልጣኑ ከክልሎች ጋር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ተቋሙ በነዳጅና ኢነርጂ ዘርፍ ላይ ብቁ ተቆጣጣሪ ለመሆን ተቋማዊ አደረጃጀት ማሻሻያዎች መደረጋቸው እና የተዘጋጀው ቁጥጥር ማዕቀፍም በካቤኒ ውሳኔ ማግኘቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም