በትምህርት ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን ማጠናከር ይገባል -ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

156

ሐዋሳ ህዳር 9/2015 (ኢዜአ) በትምህርት ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን ማጠናከርና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት   የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለፁ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ እየተካሄደ በሚገኘው 31ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባስተላለፉት መልእክት አደጋ ላይ የወደቀውን የትምህርት ጥራት ለመታደግ የተጀመሩ በርካታ የለውጥ ስራዎች ውጤት እያስመዘገቡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የታዩ ለውጦች በማጠናከር በትምህርት ስርዓቱ ላይ የገጠመንን ስብራት በመጠገን ተወዳዳሪና ሀገርን የሚያኮራ ዜጋ ለመፍጠር የተጀመረውን ርብርብ መቀጠል ይገባል ብለዋል::

ሚኒስትሩ 31ኛው ሀገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ በትምህርት ዘርፉ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ በተገኙ ውጤቶችና ባጋጠሙ ተግዳሮች ላይ የጋራ መግባባት የሚፈጠርበት መድረክ ነው ብለዋል።

ጉባኤው በዛሬ ውሎው በ2014 አፈፃፀምና በ2015 አቅጣጫዎችና የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም አጀንዳዎች ላይ ይወያያል።

 ትናንት በከፍተኛና አጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ በተደረጉ ውይይቶች ላይ ማጠቃለያና ቀጣይ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በመድረኩ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የሲዲማ ክልል ርእሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት፣ የዪኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶችና የትምህርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም