በባሌ ዞን ባህላዊ ፍርድ ቤቶች አማራጭ የፍትህ ተቋም ሆነው እያገለገሉ ነው

350

ጎባ (ኢዜአ) ህዳር 9 ቀን 2015 በባሌ ዞን የተደራጁ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለህብረተሰቡ አማራጭ የፍትህ ተቋም ሆነው እያገለገሉ መሆናቸውን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የዞኑ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች የሶስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ በሮቤ ከተማ ትናንት ውይይት ተካሄዷል፡፡

ባህላዊ ፍርድ ቤቶች የገዳ ሥርዓት መሰረት ያደረገ የሽምግልናና የዳኝነት ስራን እያከናወኑ መሆናቸውን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ማሞ ቱሲ ገልጸዋል።

በዞኑ ከ200 በሚበልጡ ቀበሌዎች የተደራጁት ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በህብረተሰቡ መካከል የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን በቅርበት በመፍታት አማራጭ የፍትህ ተቋም ሆነው እያገለገሉ ነው ብለዋል።

ህብረተሰቡ በማህበራዊ መስተጋብር የሚያገጥሙትን አለመግባባቶች ወደ መደበኛ ፍርድ ቤቶች በመውሰድ ያወጣ የነበረውን ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት ለልማት ስራው እንዲያውል እያስቻሉት እንደሆነም አስረድተዋል።

ከዚህም ባሻገር በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ ይደርስ የነበረውን የሥራ ጫና በማቃለል ለፍትህ ስርዓቱ መሻሻልም የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑም አቶ ማሞ ገልጸዋል።

ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ ባለፉት ሶስት ወራት ወደ መደበኛው ፍርድ ቤት ይመጡ የነበሩ ከ7 ሺህ በላይ የክስ መዝገቦችን በሽምግልና መፍትሄ እንዲያኙ ማድረጋቸውን በአብነት አንስተዋል፡፡

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሮብዳ ጃርሶ በበኩላቸው ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ለበርካታ የፍትህ ችግሮች መፍትሄ እያመጡ ከመሆናቸው በላይ በህብረተሰቡ መካከልም መቀራረብን እያጎለበቱ ነው ብለዋል፡፡

በባህላዊ ፍርድ ቤቶች የአፈጻጸም ሂደት ውስጥ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመለየት በዘርፉ በቀጣይ የተሻለ ሥራ ለመስራት ከመድረኩ የሚገኙ ሃሳቦችን በግብዓትነት እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች አባገዳ አብዱረህማን ሀሰን በበኩላቸው ባህላዊ ፍርድ ቤቶች እየተቀዛቀዘ የነበረውን አገር በቀል የግጭት አፈታት ስርዓት ተቋማዊ በሆነ መልኩ እንዲተገበር እድል መፍጠሩን ገለጸዋል፡፡

በባህላዊ ፍርድ ቤቶች ችሎት ውስጥ ዘመናዊ ትምህርት የቀሰመ የሰው ኃይል እጥረት እንዲቃለል አሳስበዋል።

በኦሮሚያ ክልል ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች በተጨማሪ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች እንዲቋቋሙ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 240/2013 ጨፌ ኦሮሚያ በማጽደቅ ሥራ ማሥጀመሩ ይታወሳል፡፡