የምስራቅ ሸዋ ዞን ባለፉት አራት ወራት ከ529 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

314

አዳማ ህዳር 08/2015(ኢዜአ) ባለፉት አራት ወራት ከ529 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የምስራቅ ሸዋ ዞኑ ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ ።

የዞኑ ገቢዎች ባለስልጣን ወይዘሮ በድሪያ ረሽድ ለኢዜአ እንደገለፁት የዞኑን ህብረተሰብ የልማት ጥያቄዎችን በራስ ገቢ ለመሸፈን የሚያስችል ገቢ ለመሰብሰብ እየሰራን ነው ብለዋል።

በተለይም ከመደበኛና ከመዘጋጃ ቤት ገቢ በተጨማሪ በዞኑ የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከአከራይ ተከራይ ታክስ እንዲሁም ከልዩልዩ ታክስ የተሻለ ገቢ እየሰበሰቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ዞኑ ባለፉት አራት ወራት ከ529 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ወይዘሮ በድሪያ ገልጸዋል።

ከእቅዱ አንፃር 90 በመቶ ማሳካት መቻሉን የጠቀሱት ሃላፊዋ፤ እስካሁን የተሰበሰበው ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ72 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል።

“ከህብረተሰቡ የመልማት ፍላጎት ጋር የተጣጣመ ገቢ ለመሰብሰብ አቅደናል” ያሉ ወይዘሮ በድሪያ  በዚህም በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማሳካት በሙሉ አቅማችን እየሰራን ነው ብለዋል።

በዚህም የዞኑን ልማት 40 በመቶ ለመሸፈን የሚያስችል ገቢ እንደሚሰበሰብ ተስፋ ማድረጋቸውን ሃላፊዋ ጨምሮ ገልጸዋል።