በሁለቱ አካላት የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለሀገራችን ህዝቦች ሰላም እና ሀገራዊ እድገት ያላሰለሰ ጠቀሜታ አለው

243

አዲስ አበባ ህዳር (ኢዜአ) 6/ 2015 የሰላም ስምምነቱ ለህዝቦች ሰላምና ሀገራዊ እድገት ያላሰለሰ ጠቀሜታ አለው ሲሉ የመከላከያ ውጭ ግንኙነት ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ተሾመ ገመቹ ገለጹ።

በደቡብ አፍሪካ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ ልዑክ በኬንያ ናይሮቢ ውይይት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በውይይቱም ስምምነቱ ሰላምን ለማስፈን ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ሁለቱም አካላት ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል።

ዛሬ ለወታደራዊ አታሼዎች ማብራሪያ የሰጡት ጀነራል መኮንኑ የሰሜኑን የሀገሪቱ ክፍል ግጭት በማቆም ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ መንግስት የስምምነቱ አስፈላጊነት ላይ በስፋት የተወያዩበት ሲሆን ለስምምነቱ ተፈፃሚነት ሁለቱም አካላት ጠንክረው እንደሚሰሩ ቃል ተገብቷል ብለዋል።

መከላከያ ሰራዊቱ ለሰላም ስምምነቱ ተፈጻሚነት ያለውን ቁርጠኝነት አውስተው በቀጣናው ለሚገኙ የሲቪል ማህበረሰቦች የሚደረገው የሰብዓዊ ድጋፍ ግልጋሎቱም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልገልጸዋል፡፡

የተደረሰው ስምምነት ተፈጻሚ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በገለጻው ላይ የተገኙት አካላት ኢትዮጵያ ለሰላም የወሰደችውን ቁርጠኝነት አድንቀው ለስምምነቱ ተፈጻሚነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ጄኔራል መኮንኖች የኤምባሲ ተወካዮች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወኪሎች መገኘታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም