በደብረ ብርሀን ከተማ ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የንጹህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ግንባታ ተጀመረ

278

ደብረብርሀን (ኢዜአ) ህዳር 6 ቀን 2015 በደብረ ብርሀን ከተማ ከ74 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የንጹህ መጠጥ ውሀ ማስፋፊያ ግንባታ ተጀመረ።

የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢአለ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ግንባታውን አስጀምረዋል።

የከተማው የመጠጥ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሪት መሰረት መንገሻ በወቅቱ እንደገለጹት ለማስፋፊያ ግንባታ ስራው የተመደበው ገንዘብ ከጽህፈት ቤቱ የውስጥ ገቢና በዋሪዎች ተሳትፎ የተገኘ ነው።

በአባይ ውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን በሚካሄደው የማስፋፊያ ግንባታው የአማራ ዲዛይንና  ቁጥጥር ስራዎች ድርጅት በአማካሪነት እንደሚሳተፍ ተናግረዋል።

በማስፋፊያ ግንባታው 3ሺህ ሜትር ኪዩብ ውሃ የሚይዝ የማጠራቀሚያ ጋን ተከላና የ71 ኪሎ ሜትር የውሃ ማሰራጫ መስመሮች  ዝርጋታ ስራዎች እንደሚከናወኑም ጠቅሰዋል።

ከዚህ በፊት ተቆፍረው የነበሩ ሶስት ጥልቅ ጉድጓዶችን የማገናኘት ስራም እንደሚከናወን ጠቁመው ግንባታው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አመላክተዋል ።

በማስፋፊያ ግንባታው የከተማው የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን አሁን ካለበት 53 ከመቶ ወደ 61 በመቶ ከፍ እንደሚል ጠቁመዋል ።

ማስፋፊያው የከተማዋን  የኢንቨስትመንትና  የንግድ ስራዎችን  ለማሳለጥ   አስተዋጽኦው  የጎላ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የደብረብርሀን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ካሳሁን እምቢአለ በበኩላቸው ከከተማው መስፋፋትና የኢንቨስትመንት ዕድገት ጋር ተያይዞ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ የልማት ስራዎች ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

የመጠጥ ውሀ ማስፋፊያ ግንባታው  የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

“የማስፋፊያ ግንባታው በጥራትና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ  ሙያዊ ድጋፍ  ይደረጋል“ ያሉት ደግሞ የአማራ ዲዛይንና ቁጥጥር ስራዎች ድርጅት የግንባታ ክትትል ቡድን መሪ አቶ ልዑልሰገድ ሽፈራየ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም