የእንስሳትን ዝርያ በማሻሻል የስጋና ወተት ፍላጎትን ማሟላት የሚያስችል የምርምር ውጤት ለኀብረተሰቡ ተደራሽ እየተደረገ ነው -ማዕከሉ

442

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 05 ቀን 2015የእንስሳትን ዝርያ በማሻሻል የዜጎችን የስጋና ወተት ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል የምርምር ውጤት ለህብረተሰቡ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን የደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ በእንስሳት ቁጥር ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነችና ለግብርና ምቹ የሆነ ስነ ምህዳር ያላት ሀገር ብትሆንም ዜጎች ከእንስሳት ሀብት በሚፈለገው ደረጃ ተጠቃሚ አለመሆናቸው እሙን ነው፡፡

እንደ ሀገር 15 ሚሊዮን ላሞች፣ ስድስት ሚሊዮን ግመሎች፣ ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ፍየሎች መኖራቸውን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡

ነገር ግን በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የስጋና ወተት ምርት ከፍላጎት ጋር ሲነጻጻር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

በደብረ ዘይት ግብርና ምርምር ማዕከል የእንስሳት ባዮ ቴክኖሎጂ ተመራማሪና ኃላፊ አቶ ሰይድ አሊ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አንድ ላም በቀን የምትሰጠው የወተት ምርት በአማካኝ ከአንድ ነጥብ አምስት ሊትር አይበልጥም፡፡

በኢትዮጵያ ካሉ የሚታለቡ ላሞች የሚገኘው ዓመታዊ ምርት 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ሊትር ሲሆን፤ ይህም ምርት ከዜጎች ፍላጎት 20 በመቶ የሚሆነውን ብቻ እንደሚሸፍን ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡

መንግስት በቀጣይ አራት ዓመታት በሚተገበረው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር  ዓመታዊ የወተት ምርትን ወደ 11 ነጥብ 7 ቢሊዮን ሊትር ለማሳደግ እቅድ ማስቀመጡን አስታውሰው፤ከዚህ አኳያ ማእከሉ መርሐግብሩን በእንስሳት ባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ለማገዝ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም በእንስሳት ባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር በሰው ሰራሽ ማዳቀል፣ ጽንስ በማዘዋወርና በላቦራቶሪ ውስጥ ጽንስ በመፍጠር ቴክኖሎጂ የተሻሻሉ የወተት ላም ዝርያዎችን እያወጡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዚህም ከምርምር የወጡ የተሻሻሉ የወተት ላሞች ከአርሶ አደሩ ዘንድ በቀን እስከ 20 ሊትር እየሰጡ መሆኑን ገልጸው፤ በተሻሻለ ዝርያ ብቻ የሚፈለገውን ምርት ማግኘት ስለማይቻል በእንስሳት መኖ አመጋገብና ጤና ላይ ጭምር ምርምር እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰው ሰራሽ የእንስሳት ማዳቀል ስራ የተጀመረው በ1938 ዓ.ም ቢሆንም የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች ከሁለት በመቶ እንደማይበልጡ ተናግረዋል፡፡

የጽንስ ማዘዋወር ቴክኖሎጂም በሚፈለገው ደረጃ አጥጋቢ ውጤት ሲሰጥ አለመቆየቱን አሰታውሰዋል፡፡

በመሆኑም ማዕከሉ ዓለም ላይ ያሉ ሀገራት የሚጠቀሙበትን ቴክኖሎጂ በመያዝ ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ350 በላይ የወተት ጊደሮችን አላምደናል ብለዋል ባለሙያው፡፡

የቦረና ላሞችን ከሆሊስቴይን ፍሬዥያን ጋር በማዳቀልና ዝርያቸውን በማሻሻል ምርትና ምርታማነታቸውን ማሳደግ ተችሏል ብለዋል፡፡

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዳኘ ሞጆ፤ የእንስሳት ዝርያዎችን ለማሻሻያ ማስወለጃ የኮርማ አባላዘር ቴክኖሎጂ በመጠቀም ተጨባጭ ለውጥ አሳይተናል ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮች የሚፈልጉትን የወተት ጥጃ በማዋለድ ረገድ ቴክኖሎጂው 98 በመቶ ግባችንን አሳክቷል ሲሉ ጠቁመው፤ እንደ ሀገርም በሥራው ውጤታማ ነበርን  ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ፤ የስጋና ወተት እንስሳት ዝርያዎችን ለማሻሻል የውጭ ሀገራት ደም ያላቸው ኮርማዎችን በማዳቀል ለህብረተሰቡ ተደራሽ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር መሰረት እያንዳንዱ ዜጋ በነፍስ ወከፍ በቀን የሚያስፈልገውን ስጋና ወተት እንዲያገኝ ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም