ኮርፖሬሽኑ ገበያ ለማረጋጋት 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለተጠቃሚዎች ማከፋፈሉን ገለጸ

83
አዲስ አበባ ግንቦት 11/2010 የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ገበያ ለማረጋገት የሚያስችል 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለተጠቃሚዎች ማከፋፈሉን ገለፀ። ኮርፖሬሽኑ መንግስት ድጎማ የሚያደርግባቸውን መሰረታዊ ሸቀጦች ለተጠቃሚዎች በማከፋፈል ገበያ የማረጋጋት ስራ ይሰራል። የኮርፖሬሽኑ ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ እቴነሽ ገብረሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመንግስት ድጎማ የሚደረግባቸውን ሸቀጦች ለተጠቃሚው የህብረተሰብ ክፍል እንዲሰራጭ እየተደረገ ነው። በበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት ጊዜ ገበያውን ለማረጋጋት ከ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ለዱቄት ፋብሪካዎች እንዲከፋፈል መደረጉን ተናግረዋል። ከ23 ሚሊዮን ሊትር በላይ ዘይትና ከ181 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር በኮርፖሬሽኑ አማካኝነት ለተጠቃሚዎች እንደደረሰ ወይዘሮ እቴነሽ ገልፀዋል። የአገር ወስጥ አምራቾችን ለማበረታታት በድጎማ የሚከፋፈሉ መሰረታዊ ሸቀጦችን ከአገር ውስጥ አምራቾች ለመግዛት አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል። ከውጭ የሚገባውን ምርት ቀስ በቀስ በአገር ውስጥ ምርቶች የመተካት ስራ እየተሰራ እንደሆነና በዚህም ከውጭ ተገዝተው የሚገቡ መሰረታዊ ሸቀጦችን የመተካት ስራውን 50 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ተናግረዋል። ኮርፖሬሽኑ ገበያውን ከማረጋጋት በተጨማሪ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬና ፍራፍሬ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት እንደሚሰራ ዳይሬክተሯ ጠቁመዋል። ኮርፖሬሽኑ ወደ ውጭ ከላካቸው ቡና፣ ጥራጥሬና የቅባት እህሎች 23 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን በ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት (አለ በጅምላ)፣ የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ግዢና አገልግሎት ድርጅት እና የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያ አክሲዮን ማህበርን በማጣመር በ3 ቢሊዮን 836 ሚሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመ ድርጅት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም