የመስቀልና ጊፋታን በዓል ተከትሎ ከታሪፍ በላይ ያስከፈሉ 28 አሽከርካሪዎች ተቀጡ

51
ሶዶ  መስከረም 16/12011 በወላይታ ሶዶ ዞን የመስቀልና ጊፋታን በዓል ተከትሎ ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ የተገኙ 28 አሽከርካሪዎች መቀጣታቸውን የዞኑ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ በቀለ ዋና ለኢዜአ እንደገለፁት አሽከርካሪዎቹ ሊቀጡ የቻሉት ከሶዶ ከተማ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በዓል ለማክበር የሚጓዙ መንገደኞችን ከመኸናሪያ ውጭ በመጫን ከተፈቀደው ታሪፍ በላይ ሲጭኑ በመገኘታቸው ነው። አሽከርካሪዎቹ በፈፀሙት ህገወጥ ተግባር በጠቅላላው 150 ሺህ ብር መቀጣታቸውን ተናግረዋል። በመናኸርያ አካባቢ የተደራጁ የጫኝና አውራጅ ማህበራትን በመሳተፍ ህገወጥ ተግባራትን የመከላከል ሥራ እየተካሄደ መሆኑን ምክትል ኃላፊው ተናግረዋል። በተመሳሳይ በአሉን ተከትሎ በመገበያያ ስፍራዎችና በመናኸርያ አካባቢ በስርቆትና ዘረፋ ተግባር ተሰማርተዋል ያላቸውን 15 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታውቋል ። የዞኑ ፖሊስ አዛዠ ምክትል ኮማንደር ኤፌሶን ላካይቶ እንደገለጹት ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥ ተጨባጭ ማስረጃ የተገኘባቸው  አራት ግለሰቦች በአስቸኳይ ፍርድ ቤት ቀርበው እያንዳንዳቸው በአራት ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን አስታውቀዋል። በመገበያያ አካባቢዎች ሃሰተኛ የገንዘብ ኖቶች ዝውውርን ጨምሮ የተለያዩ ህገ-ወጥ ተግባራት ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ሥራ እየተካሄደ መሆኑንም ኮማንደሩ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም