ኢትዮጵያን ከነጻ የንግድ ቀጣና የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፉን በአሰራር መደገፍ ላይ ትኩረት ተደርጓል-የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ከነጻ የንግድ ቀጣና የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፉን በአሰራር መደገፍ ላይ ትኩረት ተደርጓል-የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 3 ቀን 2015 ኢትዮጵያን ከነጻ ንግድ ቀጣና የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፉን በአሰራር መደገፍ ላይ ትኩረት መደረጉን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን አስታወቀ።
በዘርፉ አቅሙ የተገነባ የሰው ኃይል ለማፍራትና ነጻ የንግድ ቀጣናውን ለማሳለጥ የዕቃ አስተላላፊዎችና መርከብ ወኪሎች ማህበር ከትሬድ ማርክ አፍሪካ ሊሚትድ ጋር ስምምነት ፈርሟል።
በስምምነቱ መሰረት በመጀመሪያው ዙር በአዲስ አበባ በነጻ የንግድ ቀጣና አሰራር ዙሪያ ለሁለት ሳምንታት ስልጠና የወሰዱ የሎጂስቲክስ ባለሙያዎች ዛሬ አጠናቀዋል።
ባለሙያዎቹ ከግልና ከመንግሥት ተቋማት የተውጣጡ ሲሆን ነጻ የንግድ ቀጣና አሰራር ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች፣ ዕቃዎች ወደ ቀጣናው ሲገቡ መከተል ያለባቸውን ሂደቶች መሰል ጉዳዮች ላይ ስልጠና ወስደዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር የኋላሸት ጀመረ እንዳሉት ኢትዮጵያ ከነጻ የንግድ ቀጣናው በተሻለ መልኩ ለመጠቀም እየሰራች ነው።
ነፃ የንግድ ቀጣናው ከመቋቋሙ በፊት ለሁለት ዓመት ከግማሽ ያህል ጥናት መደረጉን ጠቁመው፤ ቀጥሎም ድሬዳዋ ላይ በአንድ በተካለለ ቦታ፣ ሎጂስቲክስ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት መሰረተ ልማትን ያሟላ ሆኖ መቋቋሙን አስታውሰዋል።
ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በመስኩ የሰለጠነ የሰው ኃይል ወሳኝ በመሆኑ ባለሙያዎች ስልጠና መውሰዳቸው በጎ ጅምር ነው ብለዋል።
የነጻ ንግድ ቀጣናው ዋናው ዓላማ ንግድና ሎጂስቲክስን ማሳለጥ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በመጨመር የውጭ ምንዛሬ ግኝቱን ማሳደግና መሆኑንም ነው ያብራሩት።
የዕቃ አስተላላፊዎችና መርከብ ወኪሎች ማህበር ፕሬዝዳንት ኤልሳቤት ጌታሁን በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያቋቋመችው ነጻ የንግድ ቀጣና ውጤታማ እንዲሆን ማህበሩ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለሁለት ሳምንት ሰልጥነው ዛሬ ለምርቃት የበቁት ሰልጣኞች ማህበሩ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል አንዱ መሆኑንም ገልጸዋል።
ነጻ የንግድ ቀጣና ከንግድ ባሻገር ቱሪዝምን ለማስፋፋት ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ በመሆኑ የበለጠ ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።
ማህበሩ ነፃ የንግድ ቀጣና በኢትዮጵያ አዲስ እንደመሆኑ መጠን በሚያጋጥሙ ችግርችና መፍትሄዎቻቸው ላይ በጥናት ለይቶ የመፍትሄ አካል ለመሆን እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በቅርቡም በድሬዳዋ 100 ለሚሆኑ ባለሙያዎች በነጻ ንግድ ቀጣና ዙሪያ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
በቀጣይም ማህበሩ ዘርፉን ለማዘመንና ለማሳደግ የሚረዱ ተግባራትን ለማከናወን ጥናትና ምርምር ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
የትሬድ ማርክ አፍሪካ ሊሚትድ የኢትዮጵያ ምክትል ዳይሬክተር አቶ አብነት በቀለ ነፃ የንግድ ቀጣና ለኢትዮጵያ አዲስ በመሆኑ ግንዛቤ በመፍጠር ላይ የበለጠ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ድርጅቱም የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ተደራሽ ለማድረግ ከዕቃ አስተላላፊዎችና መርከብ ወኪሎች ማህበር ጋር በትብብር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
ስልጠናውን የተከታተሉ ባለሙያዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በቀጣይ ለምንሰራው ስራ ስንቅ የሚሆን እውቀት የሸመትንበት ነው ብለዋል።