ከስደት መልስ - አገር አቀፍ የግብርና ዘር አምራች ካምፓኒ የመመስረት የታታሪነት ጉዞ

482

ዑመር መሀመድ አወል ይባላሉ፤ ውልደትና እድገታቸው ወልቄጤ ከተማ ሲሆን በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ቦረር ሜዳ ቀበሌ የሚገኘው የ"መሀመድ አወል እርሻ ልማት" ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ናቸው።

በአገራቸው ላይ ሙአለ ንዋይ አፍስሰው መስራት ከመጀመራቸው በፊት ለ10 ዓመታት በስደት ኖረዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዑመር መሀመድ በ1987 ዓ.ም ወደ አሜሪካ በማቅናት በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ሲሰሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በማመንም በ1999 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በቅተዋል።

ትኩረታቸውንም አባታቸው መሀመድ አወል በ1985 ዓ.ም ያቋቋሙትን የእርሻ ልማት ድርጅት በማጠናከርና በማስፋፋት አገርና ወገናቸውን መጥቀም በሚችሉበት ጉዳይ ላይ አደረጉ።

ጊዜ አልፈጁም ወዲያው ወደ ሰብል ልማትና ምርጥ ዘር ማምረት ተሸጋገሩ።

ቀጥለውም በስራ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶችን በመቋቋም በአገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ የሆነ የባለ ግዙፍ ምርጥ ዘር አምራች የእርሻ ልማት ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ለመሆን እንደበቁ ይገልፃሉ።

ከ30 ዓመታት በፊት 160 ሄክታር መሬት ከመንግስት በመረከብ የሰብል ልማት ስራውን አንድ ብሎ የጀመረው የእርሻ ልማት ድርጅት ዛሬ ላይ ከ1ሺ 400  ሄክታር በላይ መሬት ላይ በቆሎ፣ ቦሎቄ፣ ጤፍ፣ ሽምብራ እና ስንዴ በማምረት ላይ ይገኛል።

በቅርቡም በደቡብ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ርስቱ ይርዳው የተመራ የፌደራልና የክልል የስራ ኃላፊዎች ቡድን በእርሻ ልማቱ እየተከናወነ የሚገኘውን የምርጥ ዘር ሰብል ልማት እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።

የእርሻ ልማቱ አገር ከምትሻው ሰፊ የምርጥ ዘር አቅርቦት በተጨማሪ 2ሺህ ለሚደርሱ ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አቶ ዑመር ተናግረዋል።

ለሰራተኞቹም እስከ 2 ሚሊየን ብር የሚደርስ ወርሃዊ ክፍያ እንደሚፈጸም ጠቅሰው ጠንክሮ መስራት ለዛሬ ውጤት እንዳበቃቸው ይናገራሉ።

ከ2ሺህ ዓ.ም ጀምሮ ያካበቱትን የምርጥ ዘር ሰብል ልማት ተሞክሮ በበቆሎ ምርጥ ዘር ማሻሻያ ላይ ትኩረት በማድረግ እየሰሩ እንደሚገኙ ይጠቅሳሉ።

በተያዘው ዓመትም የእርሻ ልማት ድርጅቱ መንግስት በምርጥ ዘር ሰብል ልማት እያከናወነ የሚገኘውን ስራ ለማገዝ "ሊሙ" የተሰኘን የበቆሎ ምርጥ ዘር እያለሙ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በምርጥ ዘር ማሻሻያ ልማት ስራውም በሄክታር እስከ 50 ኩንታል የሚደርስ የበቆሎ ምርጥ ዘር ምርት ለመሰብሰብ እየጠበቁ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን የሰብል ምርጥ ዘር እጥረት ለመሙላት ድርጅቱ እያደረገ ባለው ጥረት የመንግስት እገዛ እንዳልተለያቸውም ያነሳሉ።

በዚህም የተሻሻለ የበቆሎ ምርጥ ዘርን በማልማት የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ፍላጎት ለመሙላት ሰፊ ስራ እያካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በእርሻ ልማት ድርጀቱ እየተካሄደ ከሚገኘው ሰፊ የበቆሎ ሰብል ምርጥ ዘር ብዜት በተጨማሪ ለ14 ሺህ አርሶ አደሮች የሚውል 7ሺህ ኩንታል የቀይ ቦለቄ ምርጥ ዘር ማምረት እንደተቻለ ጠቁመዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ልማትም ሌላኛው በድርጅቱ እየተከናወነ የሚገኝ የልማት ስራ እንደሆነ አንስተዋል።

በቀጣይም አኩሪ አተርን ለማልማት እቅድ እንዳላቸው ጠቁመው፤ በመጪው የበጋ ወራትም ስንዴን በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ሌሎች ባላሀብቶችም በእርሻ ኢንቨስትመንት ስራ በሚደረግ ጥረት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አማራጩን ማየት እንዳለባቸው መክረዋል።

የመንገድ እና መሰል በልማት ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመቋቋም ለአገራቸው ምርጥ ዘር አቅርቦት አሻራቸውን እያኖሩ እንዳሉ ተሞክሯቸውን በማጋራት።

በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ "የመሀመድ አወል እርሻ ልማት" ድርጅት ግንባር ቀደም አገር ዓቀፍ የምርጥ ዘር አቅራቢ ድርጅት ለመሆን እየተጋ እንደሚገኝም አመላክተዋል።

ድርጅቱ እያበለጸጋቸው የሚገኙ የሰብል ልማቶችም ትልቅ የተሻሻለ ምርጥ ዘር አቅራቢ ድርጅት እንደሚሆን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም