ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ቃልኪዳን ታደሰ በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፍ ሽልማት አገኘች

777

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ሕዳር 3 ቀን 2015 ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ቃልኪዳን ታደሰ በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ) የቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፍ ሽልማት አገኘች።

የኢትዮጵያ ‘Soil and More’ እና የጣልያኑ ‘ASTER’ ድርጅቶች በሽርክና አብሮ ለመስራት ውል ተፈራርመዋል።

ከጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ.ም አንስቶ በጣልያን ሪሚኒ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የ’Green Technology International Expo’ ትናንት ተጠናቋል።

በኤክስፖው ላይ በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲና በዩኒዶ ትብብር ድጋፍ የተደረገላቸው በአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ላይ የተሰማሩ የኢትዮጵያ ድርጅቶች መሳተፋቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ድርጅቶቹ በታዳሽ ኃይል፣ በደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፣ በአወጋገድና በመልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ናቸው።

ድርጅቶቹ በተሰማሩበት ዘርፍ ተሞክሯቸውን በኤክስፖው ላይ ያቀረቡ ሲሆን ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ ፈጠራ ክህሎትን ማሳደግ እንዲሁም በጋራ መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

ከተሳታፊ ድርጅቶች መካከል በዘላቂና አየር ንብረት ተስማሚ ግብርና ስራ ላይ የተሰማራው ‘Soil and More’ የአማካሪ ድርጅት በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም አቅም ግንባታ ዘርፍ ‘ASTER’ ከተሰኘው የጣልያን ኩባንያ ጋር በሽርክና ለመስራት ውል ተፈራርመዋል።

ከኤክስፖው ጎን ለጎን ዩኒዶ ከጣልያን መንግስት ጋር በመተባበር ለአካባቢ ተስማሚ በሆነ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ዘርፍ (Clean Tech) ውጤታማ ስራ ላከናወኑ ጀማሪ ድርጅቶች ባዘጋጀው የሽልማት መርሐ-ግብር ኢትዮጵያዊቷ ወጣት ቃልኪዳን ታደሰ ተሻላሚ ሆናለች።

የፈጠራ ባለቤቷ በኢትዮጵያ በሴቶች ንጽህና መጠበቂያ ማምረት ቴክኖሎጂ ላይ የተሰማራ ‘Happy Pads’ ድርጅት መስራችና ስራ አስፈጻሚ ናት::

በሽልማቱ ወቅት በሰጠችው ገለጻ ምርቱ ለጤንነት ተስማሚ ከመሆኑም በላይ በከፍተኛ ደረጃ የአካባቢ ብክለትንም እንደሚያስቀር ገልጻለች።

ከቃልኪዳን በተጨማሪ የአራት ሀገራት የፈጠራ ባለቤቶች ሽልማቱን አግኝተዋል።

በጣልያን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳዳር ደሚቱ ሀምቢሳ መንግስት ከዩኒዶ ጋር አረንጓዴ ቴክኖሎጂዎችን ለማስፋፋት የጀመረውን የትብብር ስራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።