ትምህርት ተደራሽ መሆኑ በአፍ መፍቻ ቋንቋችን ለመማር ረድቶናል ---በነገሌ ከተማ ነዋሪዎች

83
ነገሌ ግንቦት ግንቦት 11/2010 በአካባቢያቸው የትምህርት አቅርቦት ተደራሽ በመሆኑ  በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለመማርና ባህላቸውን ለማሳደግ የረዳቸው መሆኑን በነገሌ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ነዋሪዎቹ ይህንን የገለጹት  ዘንድሮ የሚከበረው 27ኛው የግንቦት 20ን በዓልን ምክንያት በማድረግ ኢዜአ አነጋግሯቸው በሰጡት አስተያየት ነው፡፡ በከተማዋ የቀበሌ ሶስት ነዋሪ አቶ አሰፋ ጃለታ እንዳሉት ከ20 ዓመታት ትምህርት ቤቶች በአካባቢያቸው ውስንና እነዚህም ቢሆኑ    የሚያስተምሩት  በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አልነበረም፡፡ ከዚያ ወዲህ ግን የትምህርት አቅርቦቱ እየተስፋፋ ተደራሽ በመሆኑ ልጆቻቸው መደበኛና መደበኛ ያልሆነ ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ  ተምረው መጠቀም እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ አሰፋ ሶስት ልጆቻቸው በኦሮሚኛ ቋንቋ እስከ ዩኒቨርስቲ ተምረው በመጨረስ የመንግስት ስራ መያዛቸውን ጠቅሰዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት የትምህርት በቅርበት መኖሩ ትምህርት ለመከታተል እስከ 20 ኪሎ ሜትር የሚያደረገውን የእግር ጉዞ በመቀነስ ድካምና የጊዜ ብክነት አስቀርቷል፡፡ " ተደራሽነቱ በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለመማርና ባህልን  ለማሳደግ  ረድቶናል "ብለዋል፡፡ ሌላው የቀበሌው  ነዋሪ አቶ ግርማ አንበሱም በበኩላቸው "ትምህርት በአፍ መፍቻ ቋንቋ መሰጠቱ አቅም ፈጥረን ራሳችንን በራሳችን ለማስተዳደር አብቅቶናል "ይላሉ፡፡ የገዳ ባህላዊ ስርዓት የእምነት ስፍራዎችና ሌሎችም አለም አቀፍ እውቅና ያገኙት በቋንቋቸው ተምረው ስራ በያዙና በታገሉ የኦሮሞ ልጆች ጭምር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍ መፍቻ ቋንቋ እየተሰጠ ያለው ተግባር ተኮር የጎልማሳ ትምህርትም ኑሮን በዘዴና በእቅድ ለማምራት ያስቻለ ሌላው መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ አቶ ግርማ  እንዳሉት ሶስት ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መደበኛ ትምህርት በመከታተል ላይ መሆናቸውንና ውጤታቸውም አጥጋቢ ነው፡፡ "ጥራት ላለው ትምህርት ወላጆች ፣መምህራንና የሚመለከተው አመራር ኃላፊፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል፡፡ በጡረታ የሚተዳደሩት የከተማው ነዋሪ አቶ ጎሹ ሳቀታ በሰጡት አስተያየት  ባህልን ለማስተዋወቅና ቋንቋን ለማሳደግ የትምህርት ተደራሽነት በተግባር  ለውጥ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ " በአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት መሰጠቱ የአሮሞን ህዝብ ባህልና ቋንቋ ለተቀረው አለም በማስተዋወቅ አንድ ርምጃ ወደፊት ወስዷል "ብለዋል፡፡ ከተደራሽነቱ በተጓዳኝ በትምህርት ቋንቋና ባህልን ይበልጥ ለማበልጸግ በመጽሐፍት አቅርቦት ፣በመምህራን አቅም ግንባታ፣ በተማሪዎች ክትትልና ቁጥጥር ጥራቱን ለማሻሻል ብዙ መስራት እንደሚጠይቅም አመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም