ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት 18 ሚሊዮን ቶን ምርት መያዝ የሚችሉ የግብርና ምርት ማከማቻ መጋዝኖች ያስፈልጓታል

170

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ህዳር 2 ቀን 2015 ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት 18 ሚሊዮን ቶን ምርት መያዝ የሚችሉ የግብርና ምርት ማከማቻ መጋዝኖች እንደሚያስፈልጓት የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽነር ፍሬዓለም ሽባባው ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ፣ የኢትዮጵያ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ግብርና ሚኒስቴር ለግብርና ምርቶች ማከማቻ መጋዘን ለማደራጀት የሚያስችል አውደ ጥናት አካሒደዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽነር ፍሬዓለም ሽባባው በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት አሁን ከምታመርተው እስከ አራት እጥፍ የሚደርስ የምርት እድገት ታስመዘግባለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በየዓመቱ እያደገ የመጣውን የግብርና ምርት መጠን ታሳቢ ያደረግ አገር-አቀፍ የምርት የማከማቻ ስርዓት መፍጠር ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በተለይ ማቀዝቀዣ ያላቸውን ጨምሮ ከምርቶቹ ተጨባጭ ባህሪ ጋር አብረው የሚሄዱ የምርት ማከማቻ መጋዝኖች እንደሚያስፈልጉ አንስተዋል፡፡

"በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የመጋዝን አቅም 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን ምርት መያዝ የሚችል ብቻ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ ውስጥ 22 በመቶው በባህላዊ መንገድ የተገነባ ነው" ብለዋል፡፡

በዚሁ ምክንያት በየዓመቱ ከ30 እስከ 40 በመቶው የሚመረተው ምርት ለድህረ ምርት ብክነት እንደሚዳረግ ጠቅሰው፤ ይህም በአገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ 18 ሚሊዮን ቶን ምርት መያዝ የሚችል የግብርና ምርቶች ማከማቻ መጋዝን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

መጋዝኖቹን መገንባት ብቻ ሳይሆን አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትን ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ የሚኒስቴር ዴዔታ አማካሪ ገርማሜ ጋሩማ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ መጋዝኖች እንዲገነቡ ብድር ከማመቻቸት ባሻገር ወሳኝ የግንባታ መሳሪያዎች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የበኩሉን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲዩት ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ሔኖክ መስፍን ኢንስቲትዩቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በመጋዘን እጥረት ምክንያት የሚከሰተውን የግብርና ምርት ብክነት ለመቀነስ የተለያዩ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም 44 ለሚደርሱ የህብረት ስራ ማህበራት 40 ሺህ ቶን የሚደርስ ምርት ማከማቸት የሚችል መጋዝን አስገንብቶ ማስረከቡንም ለአብነት አንስተዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ መሰል ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የጠቆሙት፡፡

ኢትዮጵያ በድህረ ምርት ብክነት በዓመት 283 ቢሊዮን ብር እንደምታጣ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም