ወጣቶች ሀገሪቱን ለማበልጸግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ጠንካራ ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል-ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

116

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ህዳር 1 ቀን 2015 የኢትዮጵያ ወጣቶች ሀገሪቱን ለማበልጸግ በሚደረገው እንቅስቃሴ በሁሉም መስክ ጠንካራ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ጥሪ አቀረቡ።

“የወጣቶች ንቁ ተሳትፎና ተካታችነት ለሰብዕና ልማት” በሚል መሪ ሀሳብ 16ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ቀን ዛሬ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተከብሯል።

በመርሃ  ግብሩ ላይ ሚኒስትሯ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ትምህርት እና የወጣቶች ያልተቆጠበ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ወጣትነትን በተለይ የማህበረሰቡ ባህል፣ ጥበብ፣ ወጎችንና ደንቦችን ከሀገር የልማት ፍላጎት ጋር በማጣጣም ማስኬድ ለውጤት እንደሚያበቃ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ መንግሥት ፈጣንና ዘላቂ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲና ሰላም የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት እንዲቻል የወጣቱን አካላዊና አዕምሮአዊ ሀብቶች ጥቅም ላይ እንዲውል እየሰራ ነው ብለዋል።

የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ በየደረጃው የሚገኙ ወጣቶች ትኩስ ጉልበታቸውንና ዕውቀታቸውን በማቀናጀት በሁሉም መስክ ጠንካራ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ሚኒስትሯ ጠይቀዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ወጣቶች ለአንድ ሀገር ልማትና እድገት  የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ መጻኢ ዕድሏን የመወሰን ከፍተኛ ሚና ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ባለቤት እንደመሆኗ ይህንን ሀብት በአግባቡ በመምራትና በመጠቀም ከድህነት መላቀቅ እንደሚቻል ገልጸዋል።

የአንድ ሀገር ሰላምና ብልጽግና የሚረጋገጠው የሁሉንም ህብረተሰብ ፍላጎት አቀናጅቶ ማስኬድ ሲቻል መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ በተለይ ወጣቱ  በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ  የበኩሉን እንዲወጣ አብክሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው ያመለከቱት።

የትምህርት ሚኒስቴር ሀገር ተረካቢና ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚጓዝ ተወዳዳሪ ዕውቀት ያለው፣ ምክንያታዊና ስነ-ምግባር የተላበሰ ወጣት ለማፍራት እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የሀገራችን ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ማጠናከር ይገባል ያለው ደግሞ ከመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች መካከል የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ቅድመ ምህንድስና ተማሪ ብዙአየሁ ማቴዎስ ነው።

ወጣቱ  ሰከን ብሎ በማስተዋል ለእኩይ ዓላማ ሳይጋለጥ አዎንታዊ ሚና በማበርከት ኢትዮጵያን ካደጉ ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ መትጋት እንደሚጠበቅበት ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም