በሽታን ተቋቁሞ ከፍተኛ ምርት የሚሰጥ አዲስ የባቄላ ዝርያ እያላመደ መሆኑን ማዕከሉ አስታወቀ

168

ጎንደር (ኢዜአ) ህዳር 1 ቀን 2015 የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል "ቆርፍድ" የተባለን በሽታ ተቋቁሞ በሄክታር 30 ኩንታል ምርት የሚሰጥ አዲስ የባቄላ ዝርያ በኩታ ገጠም እርሻ እያላመደ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ማዕከሉ በዞኑ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ያላመደውን "አሸበቃ" የተባለውን አዲሱን የባቄላ ዝርያ ለአርሶ አደሮችና አጋር አካላት በመስክ አስጎብኝቷል።

የምርምር ማዕከሉ የግብርና ስርጸት አስተባባሪ አቶ መስፍን ፈንታ በዞኑ ቆርፍድ የተባለው በሽታ እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን የባቄላ ሰብል ምርታማነት ይቀንሳል።

ችግሩን ለመፍታት በተደረገ ጥረትም ከቁልምሳ የምርምር ማዕከል የተገኘው አዲሱ የባቄላ ዝርያ ይህን በሽታ በመቋቋም በሄክታር 30 ኩንታል እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ቆርፍድ የተባለው የባቄላ በሽታ የባቄላውን ቅጠልና ግንድ በማጠውለግና በማጨማደድ ምርት እንዳይሰጥ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፣ አዲሱ የባቄላ ዝርያ ምርታማነት ከቀድሞው ዘር ጋር ሲነጻጸርም በእጥፍ እንደሚጨምር ተናግረዋል።

"በጥቁር አፈር የእርሻ መሬትና የደጋ አየር ንብረት ባላቸው አካባቢዎች እጅግ ተስማሚ መሆኑን በምርምር ማረጋጋጥ ትችሏል" ሲሉም አክለዋል።

ማዕከሉ በዞኑ 67 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በ20 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም ባካሄደው የማላመድ ሥራ አበረታች ውጤት እየተገኘ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይ ለሁሉም አርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ሊቃውንት ይሄይስ በበኩላቸው አዳዲስ የግብርና አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ በማድረግ ለአርሶ አደሩ ተጠቃሚነት በትኩረት እየተሰራ ነው።

ለክልሉ ስነ-ምህዳርና የአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑና በሽታንና ድርቅን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችን በማፍለቅ፣ በማላመድ፣ በማስፋትና በማስተዋወቅ ላይ ተመስርቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

አዲሱ የባቄላ ዝርያም በክልሉ ባቄላ አምራች በሆኑ የደጋና ወይናደጋ አካባቢዎች በስፋት በማላመድ ወደ አርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች ተዘጋጅተው እየተተገበሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

አርሶ አደር አስራት አቡሃይ እንዳሉት፣ ቆርምድ በተባለው የባቄላ በሽታ መሬታቸው ከምርት ሥራ ውጪ ከሆነ ከአራት ዓመት በላይ መሆኑን ተናግረዋል።  

"የምርምር ማዕከሉ አሁን ላይ ያመጣው አዲሱ የባቄላ ዝርያ በበሽታው ካለመጠቃቱ በላይ ቁመናውና የፍሬ አያያዙ አስደሳች ሆኖ አግኝቼዋለሁ" ብለዋል።

አርሶ አደር ታምራት ንጉሴ በበኩላቸው "ከዚህ ቀደም በግማሽ ሄክታር የዘራሁት ባቄላ በቆርፍድ በሽታ ሳቢያ አገኝ ከነበረው 7 ኩንታል ወደ 3 ኩንታል ዝቅ ብሏል" ሲሉ ገልጸዋል።

በዘንድሮ ምርት ዘመን በክረምቱ እርሻ ነባሩን ዝርያ ያለሙ አርሶ አደሮች በሽታው ባቄላቸውን ማጥቃቱን ጠቁመው፣ አዲሱ ዝርያ ግን እስካሁን በበሽታው አለመጠቃቱን እንዳረጋገጡ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም