የባዮ ጋዝ ማብላያ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያገኙ መሆናቸውን በሰሜን ሜጫ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ

248

ባህር ዳር (ኢዜአ) ህዳር 1 ቀን 2015 የባዮ ጋዝ ማብላያ ገንብተው መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ኑሯቸውን ያሻሻለ ጥቅም እያገኙ መሆናቸውን በአማራ ክልል ሰሜን ሜጫ ወረዳ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ገለጹ።

አርሶ አደሮቹ በገነቡት የባዮ ጋዝ ማብላያ ለመብራትና ምድጃ አገልግሎት ከመጠቀም ባለፈ ተረፈ ምርቱን በማዳበሪያነት ለሰብል ልማት እየተጠቀሙበት መሆኑን ተናግረዋል።

በሜጫ ወረዳ የጥቁር ባህር ቀበሌ ነዋሪ ቄስ ፈቃዱ አምሳሉ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው ዓመት በገነቡት የባዮ ጋዝ ማብላያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያገኙ ነው።

ከባዮ ጋዝ ማብለያው የሚገኘውን ሀይል ለመብራት አገልግሎትና ለምግብ ማብሰያነት መገልገል መጀመራቸው ኑሯቸውን እንዳቃለለላቸው ተናግረዋል።

ከባዮ ጋዝ ማብላያው በሚወጣውን ፈሳሽ ተረፈ ምርት ለበቆሎ ሰብል እንደማዳበሪያነት እየተጠቀሙበት መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም የሰብሉ የምርት አያያዝ ከወትሮ የተሻለ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል።

ይህም ለማዳበሪያ ግዥ ያወጡ የነበረውን ገንዘብ ከማስቀረቱ በላይ የመሬት ለምነት እንዲጨምር የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል።

የቀበሌው ነዋሪ ወይዘሮ ማንጠግቦሽ ሃይሌ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት የተገነባላቸውን ባዮ ጋዝ ለመብራት፣ ለምግብ ማብሰያ እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ለከሰልና ለእንጨት የሚያወጡትን ወጭ ከማስቀረቱ በሻገር በጭስ ምክንያት "የታመመው ዓይኔ ይጠፋ ይሆን" የሚል ስጋታቸውን እንደቀነሰላቸው ነው የተናገሩት።

"መብራት መኖሩ ተማሪዎችም እስከ ሌሊት ድረስ በማንበብ በትምህርታቸው እንዲበረቱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል" ያሉት ወይዘሮ ማንጠግቦሽ፣ ሌሎችም የባዮ ጋዝ ማብላያ በመገንባት እንዲጠቀሙ መክረዋል።

በሰሜን ሜጫ ወረዳ ስንዴን ብቻ ሳይሆን የበዮ ጋዝ ኢነርጂን በማስፋፋት አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ማድረግ መጀመሩን የገለጹት ደግሞ የወረዳው አስታዳዳሪ አቶ አንተነህ ወንዴ ናቸው።

በአንድ አካባቢ የባዮ ጋዝ እና የዘመናዊ መጸዳጃ ቤትን አስተሳስሮ በመጠቀም የባዮ ጋዝ ሃይልና የባዮ ማዳበሪያ ከማምረት ባለፈ ተረፈ ምርቱን ለእርሻ በማዋል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

እስካሁንም በወረዳው 551 ባዮ ጋዝ ማብላያዎችን በመገንባት በታዳሽ ሃይል ላይ የተመሰረተ የኩታ ገጠም የኢነርጂ ልማት እያካሄዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው በበኩላቸው እንዳሉት፣ የገጠሩን ማህበረሰብ የባዮ ጋዝ ተጠቃሚ በማድረግ የተያዘውን የአረንጓዴ ልማት ስትራተጂ ለማሳካት እየተሰራ ነው።

ሳይንሳዊ ጥናትን ጠቅሰው እንደገለጹት አንድ ባዮ ጋዝ ማብላያ መገንባት ሁለት ቶን የማገዶ እንጨትን መቆጠብና ከአራት ቶን በላይ የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀትን ማስቀረት ነው።

"በተጨማሪም ከ270 ኩንታል በላይ ኮምፖስትን በመተካት የአርሶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ያግዛል" ብለዋል።

መንግስት የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ፣ በማስገንባትና የጥገና ሥራ በማካሄድ በኩል ከረጂ ድርጅቶችና አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር ተደራሽነቱን ለማስፈት እየሰራ መሆኑን ሃላፊው አስገንዝበዋል።

በአማራ ክልል በአጠቃላይ 77ሺህ 800 አርሶ አደሮች ባዮ ጋዝን ለመብራት፣ ለምግብ ማብሰልና ለማዳበሪያ አገልግሎት በመጠቀም ኑሯቸውን እያሻሻሉ መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መራጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም