የሐረሪ ክልል አርሶ አደሩን በዘመናዊ የግብርና አሰራር ምርታማነቱን ለማሳደግ እየሰራ ነው

127

ሐረሪ (ኢዜአ) ጥቀምት 30 ቀን 2015 በሐረሪ ክልል አርሶ አደሩ ዘመናዊ የግብርና አሰራርና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ገለጹ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር እና የግብርና ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ በክልሉ በኩታገጠም የሚለማ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ዛሬ በኤረር ወረዳ ቂሌ ቀበሌ ተገኝተው አስጀምረዋል።

በእዚህ ጊዜ እንደገለጹት በክልሉ በ2014 በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ በተደረገው የበጋ መስኖ ሥራ 3 ሺህ ሄክታር ማሳ ሊለማ ችሏል።

ከልማቱ የተገኘውን ምርት አርሶ አደሩንና ሸማቹን በማገናኘት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግብይት እንዲፈጽሙ መደረጉንም አስታውሰዋል።

ዘንድሮ በክልሉ በ150 ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እንደሚከናወን የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ፣ ዛሬ በ47 ሄክታር መሬት ላይ የተጀመረው ልማት የእዚህ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የስንዴ ልማት ሥራው በኩታገጠም የእርሻ ዘዴ እንደሚካሄድ ጠቁመው፣ በእዚህም የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

"ለአርሶ አደሩ አስፈላጊውን ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ከማቅረብ ጀምሮ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ትኩረት ተድርጓል" ሲሉም አክለዋል።

ወይዘሮ ሚስራ አያይዘው እንደገለጹት የስንዴ ልማቱን ጨምሮ በክልሉ በበጋ ወቅት 4ሺህ ሄክታር መሬት በተለያየ አትክልት እና ሰብል በማልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

አርሶ አደሩ በክላስተር ተደራጅቶ ወደስራ መግባቱ አብሮነቱን ከማጎልበት ባሻገር ወጥ የሆነ ምርታማነት እንዲኖር እና የጋራ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንፃር ሚነው የጎላ መሆኑንም ወይዘሮ ሚስራ ገልጸዋል።

በክላስተር ተደራጅተው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከጀመሩ የኤረር ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል ከማል ጣሂር በክላስተር ተደራጅተው ልማቱን እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አንደ አርሶ አደሩ ገለጻ ለልማቱም የክልሉ ግብርና ቢሮ በአጭር ጊዜ የሚደርስ ምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ እያቀረበላቸው ነው።

የግብርና ባለሞያዎችም በማሳ በመገኘት አስፈላጊውን እገዛ እያደረጉላቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር አብዱላሂ አህመድ በበኩላቸው ካሁን ቀደም ከማሳው አጥጋቢ ምርት ያገሹ እንዳልነበር አስታውሰው አሁን ላይ በክላስተር ተደራጅተው ወደ ስራ በመግባታቸው የተሻለ ምርት ለማግኘት ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም