በኢትዮ- ኬንያ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ኃይል የማስተላለፍ የሙከራ ሥራ በስኬት ተከናወነ

176

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥቅምት 29/2015 በኢትዮ- ኬንያ የኮንቨርተር ስቴሽንና የማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ላይ ኃይል የማስተላለፍ የሙከራ ሥራ ዛሬ በስኬት መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ አያሌው እንደገለጹት በኢትዮ ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ላይ ኃይል የማስተላለፍ የሙከራ ሥራ በይፋ ተጀምሯል፡፡

የሙከራ ሥራው መሳካቱ በቅርቡ ከኬንያ ጋር የሚጀመረው የኃይል ትስስር ሥራ በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚከናወን አመላካች መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከቀናት በፊት የኮሙዩኒኬሽን ሲግናል በመላክ ሲግናሉን ከኬኒያ ኔትወርክ ጋር ማገናኘት መቻሉን አቶ ቴዎድሮስ ጠቁመዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ኃይል ማስተላለፍ ሲጀምር በህብረተሰቡ ላይ አደጋ እንዳያደርስ መስመሩ ከሚያልፋባቸው ዞኖች በየደረጃው ከሚገኙ የሥራ ኃላፊዎችና ከወረዳና ከቀበሌ ተወካዮች ጋር የውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች መካሄዳቸውን አስታውሰዋል፡፡

በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ምክንያት የሙከራ ሥራ እየተከናወነ ባለበት ወቅት ምንም አደጋ አለማድረሱንም አቶ ቴዎድሮስ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮ- ኬንያ የማስተላለፊያ መስመርና ኮንቨርተር ስቴሽን ፕሮጀክት በ334 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተገነባ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 214 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላሩ ለኮንቨርተር ስቴሽኑና ለግራውንድ ኤሌክትሮድ መስመር የግንባታ ሥራ እንዲሁም 120 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ለማስተላለፊያ መስመሩ የዋለ ነው፡፡

የግንባታ ሥራው በ2008 የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት እስከ 2000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፍ አቅም እንዳለው በፕሮጀክቱ ሲነየር ፕሮጀክት ኢንጂነር ኃይለማርያም ሞገስ ገልፀዋል፡፡

የማስተላለፊያ መስመሩ የግንባታ ሥራ እ.አ.አ በ2018 እንዲሁም የኮንቨርተር ስቴሽኑ እ.አ.አ በታህሳስ 2021 መጠናቀቁን የኢትዮጵያ የኤሌክተሪክ ኃይል በማህበራዊ ትስስር ገጹ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም