ከጉባኤዎቹ የህዝብን ጥያቄዎች የሚመልሱና ሀገራዊ ለውጡን የሚያስቀጥሉ ውሳኔዎች እንደሚጠበቅ ምሁራን ገለጹ

104
አክሱም መስከረም 15/2011 ከህወሓት/ኢህአዴግ ጉባኤዎች የህዝቡን ጥያቄዎች የሚመልሱና በሀገር ደረጃ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቀሴ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ውሳኔዎች እንደሚጠበቅ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ  ምሁራን ገለጹ፡፡ ጉባኤዎቹን አስመልክቶ የኢዜአ ሪፖርተር ያነጋገራቸው  ምሁራኑ እንዳሉት የክልሉን መንግስት ከሚመራው ህወሓት የህብረተሰቡን  የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚመልሱ ውሳኔዎች ይሻሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አጽብሃ ተክለ በሰጡት አስተያየት ከህወሓት ጉባኤ " በተለይ የሃሳብ ብዙሃነትን ማሰተናገድ፣ በክልሉ ያለውን ሰላም ለማስቀጠልና የሚታዩ የፖለቲካ ግድፈቶችን የማስተካከል ውሳኔ እጠብቃለሁ "ብለዋል። የድርጅቱ ፖሊሲ፣መመሪያና ደንብ የሚያውቁ ወጣቶችና ሴቶችን ወደ አመራር መመጣት የሚችሉበት የመተካካት አሰራር ተግባራዊ የማድረግ ውሳኔም እንዲሁ። የክልሉ ልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚመልሱ አቅጣጫዎች  መኖር እንዳለባቸውም  መምህር አጽብሃ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ "ከክልሉ ውጭ ያሉ ተወላጆችን ደህንነት እንዲጠበቅና  ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን እንዲከበር ህወሓት አጥናክሮ የሚቀጥልበት ውሳኔ መፍጠር ይጠበቅበታል" ብለዋል። ከኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤም  የሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ለውጥ  ወደ ተሻለ ደረጃ  የሚያሸጋግር አመራር ማምጣት የሚያስችል ውሳኔ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል። የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከኢህአዴግ ጉባኤ ጠንካራ ውሳኔ እንደሚያሻም ጠቁመዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው የፖለቲካ ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሓዱሽ ረዳኢ በበኩላቸው፣  ከህወሐት/ኢህአዴግ/ ጉባኤዎች የለውጥ እና የችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫ ሊኖር እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ህወሓት በተዋረድ ያሉትን መዋቅሮች  በአግባቡ በመፈተሽ  ለችግር ምንጭ የሆኑ የህዝብ ጥያቄዎች የማይመልሱ አመራሮች በተሻሉ  የሚተካ ከጉባኤው እንደሚጥብቁ ተናግረዋል። ህወሓት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ጠንክሮ ሊሰራበትና ውስጣዊ  የዴሞክራሲ ግንባታ የሚጠናከርበት ሁኔታ ለማመቻቸት የሚያስችል ውሳኔ ማተላለፍ እንዳለበትም አመልክተዋል። "የህዝቡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበት ሁኔታ ለመፍጠር ከጉባኤው ትልቅ የፖለቲካ ውሳኔ ይጠበቃል "ብለዋል። ሀገሪቱን ከሚመራው ኢህአዴግ ጉባኤም ጉድለቶችና ለውጡን በመገምገም በአሰራርና በህግ እንዲደገፉ በተለይ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበር የሚያስችሉ ውሳኔዎች እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። የተጀመረው የኢትዮ- ኤርትራ የሰላምና የንግድ ግንኙነትም ቀጣይነት እንዲኖረው ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ  እና ፖለቲካዊ መርህ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሚያስችል ተጨማሪ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች እንደሚጠበቁም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም