የአካባቢያችንን ሰላም በማስጠበቅ ለሀገራዊ ለውጡ ቀጣይነት የድርሻችንን እንወጣለን -በሐረማያ ወረዳ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች

56
ሐረር መስከረም 15/2011 የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ በሐረማያ ወረዳ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለፁ። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከወረዳና አካባቢው ለተውጣቱ ከ200 በላይ አባገዳዎች፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በገዳ ስርዓት እሴት፣ ግጭት አፈታትና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳይዎች ላይ የሁለት ቀን ግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል። የስልጠናው ተሳታፊዎች " የአካባቢያችን ሰላም የሚጠበቀው በመንግስት ብቻ ሳይሆን በሁላችን ተሳትፎ በመሆኑ የበኩላችንን እንወጣለን " ሲሉ የተስማሙበትን የጋራ ውሳኔ አስተላልፈዋል ። በተለይም ወጣቱ በተሳሳተ አቅጣጫ እንዳይሄድ በመምከር የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅና የለውጡ አራማጅ እንዲሆን ለማድረግ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተሳታፊዎቹ ተስማምተዋል። ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አባገዳ አህመዲን ሙክታር አብዱላሂ በሰጡት አስተያየት "ወላጆች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ከስነ- ምግባር ወጣ ያሉ ወጣቶችን የመመለስ ከፍተኛ ኃላፊነት አለብን " ብለዋል ። “በአካባቢው ግጭት ሲከሰት የማረጋጋት፣ የማስተማርና የመምከር ሥራ ስንሰራ ቆይተናል" ያሉት ደግሞ በወረዳው የአዴሌ ቀበሌ 01 ነዋሪና የአገር ሽማግሌ አቶ ተስፋዬ ለማ ናቸው ። "ወደፊትም ወጣቱን በመገሰፅና በመምራት የአካባቢውን ሰላም እንዲጠብቅ የማብቃት ሚናችንን በአግባቡ እንወጣለን " ሲሉ ተናግረዋል ። የሐረማያ ከተማ ነዋሪ ወጣት እዮብ አብዱሌ በበኩሉ "ወጣቱ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማራመድ የሚፈልጉ ፀረ- ሰላም ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን ተቀናጅተን እየሰራን ነው" ብሏል። ከመንግስት አካላት፣ ከአባ ገዳዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር እየተገናኙ በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ የጀመሩት ውይይት የአካባቢያቸውን ፀጥታና ሰላም ለመጠበቅ እንደረዳቸው ተናግሯል። የሐረማያ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር አበዛ ደረጀ በበኩላቸው ያለህብረተሰቡ ተሳትፎ የወንጀል መከላከል ስራ ማካሄድ እንደማይቻል ተናግረዋል ። እንደ ኢኒስፔክተሩ ገለጻ ስልጠናው የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎቸ፣ የሀይማኖት አባቶችና ወጣቶች በሰላም፣ በመቻቻልና በእርቅ ማውረድ የሚያከናውኗቸውን  ስራዎችን ለማጎልበት አስተዋፆው የጎላ ነው። የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጀይላን ወልዩ የዩኒቨርሲቲው ህልውና በመንግስትና በህዝብ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል ። "የዩኒቨርሲቲው የመማር ማተማር፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉት የአካባቢው ሰላም እስከተረጋገጠ ድረስ ብቻ ነው" ብለዋል ። የአካባቢው ማህበረሰብ አባላት የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታትና መልካም እሴቶችን ለማጎልበት በሚያከናውናቸው ስራዎች ዩኒቨርሲቲው ተጠቃሚ እንደሚሆንም ተናግረዋል። በማህበረሰቡ የሚከናወኑ ስራዎች በእውቀት ላይ የተመሰረቱና ቀጣይነት ያላቸው እንዲሆኑ በማሰብ ስለጠናው መዘጋጀቱንም ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም