በቅርቡ በቤኒሻንጉል ጉመዝ ክልል በተከሰተው ግጭት ተጠርጣሪዎች ላይ የሚደረገው ምርመራ ተጠናቋል— የክልሉ ፍትህ ቢሮ

2569

አሶሳ መስከረም 15/2011 በቅርቡ በቤኒሻንጉል ጉመዝ ክልል አሶሳና አከባቢው በተከሰተው ግጭት በ21 ሰዎች ግድያ ላይ በተሳፉ ተጠርጣሪዎች ላይ የሚደረገው ምርመራ እየተጠናቀቀ መሆኑን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ሃላፊ አቶ መሃመድ ሃሚድ እንዳስታወቁት በክልሉ ከሰኔ 16 እስከ 21 / 2010 ዓ.ም. በአሶሳ፣ ሸርቆሌ እና ቶንጎ ከተሞች በተከሰቱ ግጭቶች 21 ሰዎች ሲሞቱ በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል።

በአሶሳ ከተማ በነፍስ ማጥፋት ወንጀልና በዝርፊያ ከተጠረጠሩ 117 ከሚጠጉ ሰዎች መካከል 53 ተይዘው ቃላቸውን መስጠታቸውንም ተናግረዋል።

ከመካከላቸውም 20ዎቹ በፍርድ ቤት 17 ደግሞ በፖሊስ ጥያቄ ዋስትና ሲያገኙ 16ቱ ተጠርጣሪዎች በጊዜ ቀጠሮ በማረሚያ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

በሸርቆሌ ከተማ ግጭት የተጠረጠሩ 47 ሰዎች ላይም ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ መዝገቡ ለአቃቢ ህግ በማቅረቡ ክስ እንደተመሰረተ አመልክተዋል፡፡

በማኦኮሞ ልዩ ወረዳ ቶንጎ ከተማ በተከሰተው ግጭት የተጠረጠሩ ሰባት የፖሊስ እና ሶስት የልዩ ሃይል አባላት ላይም ምርመራው እየተጠናቀቀ ሲሆን በጥቂት ቀናት ውስጥ ክስ እንደሚመሰረት ተናግረዋል።

የምርመራውን ሂደት በ26 ቀናት ለማጠናቀቅ ታቅዶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ መሃመድ በክልሉ ሌሎች አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ የምርመራው ሂደት መጓተቱን አብራርተዋል፡፡

ከአሶሳና አካባቢው በተጨማሪ በቅርቡ ኦዳቢልድግሉ፣ ጉባ እና ሰዳል ወረዳዎች በተከሰቱ ግጭቶች የ30 ሰዎች ህይወት ማለፉን በርካታ ሰዎችም መፈናቀላቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት በግድያ እና ዝርፍያ ወንጀሎቹ የተጠረጠሩ 70 የሚጠጉ ሰዎች ላይ ምርመራ እየተካሄደ ነው፡፡

የፍትህ ሥራ ወንጀለኞችን ለህግ ከማቅረብ ባሻገር ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን መለየት መሆኑን የገለጹት ሃላፊው “የምርመራው ሂደት ያለማንም ጫና በገለልተኝነት  እየሠራን ነው” ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ እጁ ያለበት ማንኛውም አካል ለህግ የበላይነት መከበር ሲባል እንደማይታለፍ የጠቆሙት አቶ መሃመድ ወንጀሎቹን የማጣራቱ ሥራ ከፌዴራል መንግስትና እና ከአጎራባች ክልሎች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ ባለፉት ሶስት ወራት የተከሰቱ ግጭቶችን የመመርመሩ ሥራ ከወንጀሉ ጀርባ የሚገኙ አካላት የተጠቀሙበት ስልት ውስብስብ እንዳደረገው አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ ግጭቶች ሲከሰቱ በብሄር መካከል ነው በሚል ከመረበሽ ይልቅ በጥንቃቄ በመመልከት በህዝቦች መካከል ያለው መልካም ግንኙነት ለማስቀጠል ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።