የትራንስፖርት ባለስልጣን 18 አገልግሎቶችን በኢ-ሰርቪስ መስጠት ጀመረ

107
አዲስ አበባ መስከረም 15/2011 የትራንስፖርት ባለስልጣን 18 አይነት አገልግሎቶችን በኤሌክትሮኒክ (ኢ-ሰርቪስ) መስጠት ጀመረ። የዜጎች እንግልትን ጨምሮ ከፍተኛ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች ከተንሰራፋባቸው የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል የትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ አንዱ መሆኑ ይነገራል። የተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ የአሰራር ሂደት ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ ከሚቀርብባቸው መካከል ነው። ዛሬ ይፋ የሆነው በኮምፒውተር ስርዓት የተደገፈ አዲስ የአገልግሎት መስጫ የቆዩ የህዝብ ቅሬታዎች የሚመልስ ከመሆኑም በላይ የሙስና ቀዳዳዎችንም እንደሚደፍን ታምኖበታል። ባለስልጣኑ ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በትብብር ያዘጋጀው የኤሌክትሮኒክስ መተግበሪያ ደንበኞች በአካል መገኘት ሳይጠበቅባቸው ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸውን ወይም ኮምፒውተሮቻቸውን በመጠቀም ብቻ አገልግሎት ለማግኘት ያስችላቸዋል። አገልግሎቱ የተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫና ምዝገባ፣ የጭነት ትራንስፖርትና የህዝብ ትራንስፖርት ተብለው በተከፈሉ ሶስት ንኡስ ዘርፎች የተለየ ነው። ማንኛውም የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን አገልግሎቶች የሚሻ  'www.eservices.gov.et' የሚለውን አድራሻ በመጠቀም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይችላል ተብሏል። የትራንስፖርት ባለስለጣን ዋና ዳሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ እንዳሉት፤ አሰራሩ የደንበኞችን እንግልት ለመቀነስና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። የአገሪቱን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማሳደግ የተያዘው እቅድ አንድ አካል የሆነው ይህ አሰራር አድሏዊ አሰራርን ያስቀራል ተብሎ ይጠበቃል። የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሲሳይ ቱሉ በበኩላቸው አሰራሩን በ34 የመንግስት ተቋማት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል። ፍትህ፣ ታክስ ዘርፎችን ጨምሮ ከፍተኛ የህዝብ አገልግሎት መስተጓጎልና አንግልት የሚስተዋልባቸው ተቋማት ውስጥ ተመሳሳይ ዘመናዊ አሰራር ለመዘርጋት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም