የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች በታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ዙሪያ እየተወያዩ ነው

102
አዲስ አበባ መስከረም 15/2011 የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች በታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላል ዙሪያ አዲስ አበባ ላይ ውይይት እያካሄዱ ነው። ውይይቱ የሶስቱ አገራት መሪዎች በቤጂንጉ የቻይና-አፍሪካ ፎረም ላይ ባካሄዱት የሶስትዮች ውይይት ባሳለፉት ውሳኔ መሰረት መሆኑ ተገልጿል። የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የግብጹ አቻቸው ዶክተር ኢንጂነር አብደል አቲ እና የሱዳኑ የውሃ ሃብት መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ኢንጂነር ከድር ቀሲም አል ሰይድ ናቸው ውይይቱን የጀመሩት። ባለፈው ግንቦት በአዲስ አበባ በተካሄደው የመሪዎችና የሚኒስትሮች ውይይት የውሃ አሞላሉን የሚመረምር ከሶሰቱም ሀገራት የተውጣጣ የተመራማሪዎች ቡድን  ተቋቁሞ ስራ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን የዛሬው ውይይትም የኮሚቴውን የምርመራ ውጤት አድምጦ ይመክራል ተብሏል። የተመራማሪ ቡድኑ ስራውን በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ለማወቅ ተችሏል። በውይይቱ ላይ የተመራማሪዎች ቡድንም ተሳታፊ አንደሚሆን ተገልጿል። የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በውይይቱ መግቢያ ላይ የተማራማሪዎቹ ቡድን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል ላይ ጠቃሚ የሆነ ጥናት አድርጓል ብለዋል። ሚኒስትሩ አክለውም ውይይቱ የጥናቱ ውጤት የሚጠናቀቅበትን መንገድ እንዲሁም ልዩነቶች ካሉ ልዩነቶችን የምንፈታበት ይሆናል ብለዋል። ወደፊት ሀገራቱ በጋራ ስለሚሰሩበት ሁኔታም ይመከራል ብለዋል። የሱዳኑ አቻቸው ኢንጅነር ከድር ቃሲም አል ሰይድ በውይይቱ የተመራማሪው ቡድን ይዞት የመጣው ውጤት ላይ ልዩነት ቢኖርም እንኳን ልዩነቶችን ለመፍታት ዝግጁ ነን ብለዋል። ከዚህ በፊት በተደረጉ ስምምነቶች መሰረት ልዩነቶችን በማጥበብ ወደፊት መራመድ አለብን ብለዋል። የግብጹ የውሃና መስኖ ሚኒስትር ዶክተር መሀመድ አብደል አቲ በበኩላቸው ውይይቱ ሀገራቱ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያመላክትና በብሄራዊ ቴክኒካል ኮሚቴው ላይ አስተያየቶች የሚሰጥበት ነው ብለዋል። የግድቡ ውሃ አሞላል የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን በማይጎዳ መልኩ በሚሞላበት ሁኔታ ላይ  እንደሚሰሩም ገልፀዋል። በሶስትዮሽ ውይይቱ መጨረሻ በግብፅ በኩል ልዩነቶች በሌላ በሶስተኛ ወገን አደራዳሪነት እንዲፈታ የነበራትን አቋም በመተው በግድብ አሞላልና የውሃ አለቃቀቅ ላይ ራሱን የቻለ ሳይንሳዊ ጥናት ለማካሄድ ከሶስቱ አገሮች ከእያንዳንዳቸው አምስት አባላት የሚወከሉበት አንድ ቡድን ማቋቋማቸው ይታወሳል። የሁሉም አገሮች መሪዎች ሶስቱም አገሮች እንደ አንድ ሀገር እንዲሰሩ፣ፈጠራ የታከለበት የመፍትሄ ሃሳቦች እንዲያመነጩ እንዲሁም አገራቱን የሚያስተሳስሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንዲያከናውኑ ነበር አቅጣጫ የተቀመጠው። የአገሮቹ መሪዎች ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜ ተራ በተራ በመዲናቸው እንዲካሄድ ሚኒስትሮቹ ከመግባባት ላይ ደርሰዋል። የሀገራቱን ግንኙነት ዘላቂ ለማድረግም የመሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት ፈንድን ለማቋቋም እንዲቻል የሶስቱ አገሮች የሚመለከታቸው የውሃ ኃላፊዎች እየሰሩ እንደነበር ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም