ታላቁ ዓሊ

387

በብርሃኑ አለማየሁ

ዘመን በማይሽረው መረዋ ድምጹ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ኅብረትን፣ ጽናትንና ባህልን ያቀነቀነው ታላቁ ድምጻዊ አሊ መሀመድ ሙሳ ወይም በመድረክ ስሙ ዓሊ ቢራ የዘመናዊ የኦሮሚኛ ሙዚቃ ታሪክ ሲነሳ ትልቅ አስተዋጽኦ ካበረከቱ አቀንቃኞች መካከል ስሙ ከፍ ብሎ ይጠራል።

አርቲስት ዓሊ ቢራ ከሀምሳ ዓመታት በላይ በተሻገረው የሙዚቃ ሕይወቱ ያልዳሰሰውና ያልነካው ጉዳይ የለም ይልቁኑም ስራዎቹ የአዛውንት ትዝታ፣ የወጣቶች ተስፋና የማህበረሰብ ማንቂያ ሆነዋል።

ከአድማጭ ጆሮ ከወዳጆቹ አንደበት ሳይጠፉ በኢትዮጵያውያን ልብ በፍቅር የሚቀነቀኑት የዓሊ ሙዚቃዎች እርሱ ዛሬ በሕይወት ባይኖርም ትውልድ የሚታነጽባቸው ትምህርት ቤቶች ናቸው።

በዚህ ይዘት ስር እስከ ዛሬ የዘለቁት ስራዎቹ አሊን እንዳንረሳው አድረገውታል፤ በሕይወት ቢለይም በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ሕያው ሆኖ እንዲኖር አድርገውታል።

የዓሊን ሕያውነትና የሐዘን መልዕክቱን የገለጸው አርቲስት ሰርጸ ፍሬስብሐት “ዓሊ፥ የጥዑም ድምጽ ባለተሰጥዖነቱ ብቻ አልነበረም የሚያስደንቀው። ፈረንጆቹ "genius" የሚሉት ዓይነት የሙዚቃ ሰው ስለነበረም እንጂ” ብሏል።

አክሎም ሙዚቃን፤ በዕውቀት ምሥጢሯን ዐውቆ የተጫወታት ታላቅ ድምጻዊ፣ ዓሊ ሞሐመድ "ብራ" ነበር ሲልም አመልክቶ ዓሊ፥ ሙዚቃዎቹን ራሱ ያቀናብራል፣ ዑድ፣ ጊታር፣ ኪቦርድ፣ ፒያኖ፣ አኮርዲዮን እና ሐርሞኒካ አሳምሮ ይጫወታል” ሲል ሁለገብነቱን መስክሯል።

አሊ ከክብር ዘበኛ፣ ከአይቤክስ፣ ከኢትዮ ስታር ሙዚቀኞች ጋር በሠራቸው የሙዚቃ ሥራዎች፣ አድማጮቹ ብቻ ሳይኾኑ፣ አብረውት የሠሩት ሙዚቀኞች ኹሉ እንደተደነቁበት፣ ሙዚቃን እንዳስከበረ ዕድሜ ልኩን የኖረ ታላቅ ሙዚቀኛ ነበር።

በሙዚቃ ስራዎቹ ባለ ራዕይነቱንና ህዝባዊነቱን ያስመሰከረው ዓሊ ከመለያየት ፍቅርን ከጸብ አንድነትን በሚያመለክቱ ሰራዎቹ ትምህርት ሰጥቷል።

”Barnootaa ammas Barnootaal” መማር አሁንም መማር” በሚለው ኦሮሚኛ ሙዚቃውም ዕውቀት የአድገት ብርሃን መሆኑን ከዘመናት ቀድሞ አስገንዝቧል።

በኦሮሚኛ ቋንቋም ሆነ በሌሎች ቋንቋዎች በተጫወታቸው ሙዚቃዎችም ሳይሰለች የሚደመጠው አሊ በሙዚቃዎቹ በሚያስተላልፋቸው መልዕክቶች የተነሳ ያለ ቋንቋ ገደብ የብዙኃን አንደበት የሚያቀነቅነው ሁለገብ ሙያተኛ ነው።

አንጋፋው አርቲስት ዓሊ ቢራ ከ260 በላይ ሙዚቃዎችን ያቀነቀነ ሲሆን ስድስት አልበሞችን በማሳተም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ዘላለማዊ አሻራውን አኑሯል።

ከድሬዳዋ ገንደቆሬ ተነስቶ በአለም አደባበይ በሙዚቃ ታሪክ የሰራው አሊ የኦሮሞን ባህልና ማህበረሰባዊ እሴት ከማስተዋወቅ ባለፈ የህዝብ ድምጽ ሆኖ ሰላማዊ ትግል አካሂዷል።

የተቸገሩ ወገኖችን፣ ታዋቂ ግለሰቦችንና መጠጊያ የሌላቸውን ከመርዳት ፋውንዴሽን እስከ ማቋቋም የደረሰው የአሊ ህዝባዊ ልብ ዛሬም…በመረዋ ድምጹ አጠገብ እንዳለ ወዳጅ እየተናፈቀ ይደመጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም