በሰላም ስምምነቱ ዙሪያ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት የተሰጠ ማብራሪያ

150

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ላለፉት 24 ወራት የዘለቀውን ጦርነት ለማስቆም የሚያግዝ የሰላም ስምምነት በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ተፈርሟል፡፡

መንግስት ግጭቱ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ለሰላም ዕድል ለመስጠት ተደጋሚ ሙከራዎችን ሲያደርግ መቆየቱም ይታወቃል፡፡

በዚህም በአካባቢው የተፈጠረውን ግጭት ለማቆም የሚረዳ የሰላም ስምምነት በማድረግ ዜጎችን ከገጠማቸው ችግር ለማላቀቅ ቁርጠኝነቱን በተደጋጋሚ አሳይቷል።

ይህን ተከትሎ ከሰሞኑ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ሲካሔድ የቆየው የሰላም ስምምነት ህግ መንግስታዊ ስርዓቱን ባከበረ እና  የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ባስጠበቀ መልክ መጠናቀቁ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትርና የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ገለፃ አድርገዋል።

አምባሳደር ሬድዋን በገለፃቸው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ባስጠበቀ መልኩ ዘላቂ ግጭት ማቆምና ዘላቂ ሰላም ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።

ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም ሲባል በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የቆየውን የግጭት ምዕራፍ በመዝጋት በሰላምና በመግባባት ለመኖር ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልፀዋል።

"የሰላም ስምምነቱ ግጭቱ በሰላም የሚቋጭበትን ሁኔታ የሚዳስስ ሲሆን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት እንድነት የሚያጸና ህገ መንግስቱን ያከበረ የስምምነት ነጥቦችን ያቀፈ ነው" ሲሉም አብራርተዋል።

ስምምነቱ በአጠቃላይ የተኩስ ማቆም፣ የህወሃት ሀይሎችን  ትጥቅ  ማስፈታት፣  በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም፣ መሰረታዊ አገልግሎት ማስጀመር፣ መልሶ ግንባታንና የመሳሰሉ ጉዳዮችን የሚዳስስ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በመንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ወደ መሬት ለማውረድ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውንም ገልፀዋል።

በስምምነቱ መሠረት የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት የኮሙኒኬሽን ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

ወታደራዊ አመራሮቹ በቀጣይ ቀናቶች  በኬንያ ናይሮቢ  ተገናኝተው  ስምምነቱን  ተግባራዊ ለማድረግ ውይይት እንደሚጀምሩ የሚጠበቅ መሆኑን ገልፀዋል።

"በእኛ በኩል የሰላም ስምምነት ሂደቱን ወደ ፊት ለማራመድ ያለንን ዝግጁነት እያሳየን ነው። በሌላ በኩል በስምምነቱ መሰረት የሁለቱ ወታደራዊ አመራሮች በአምስት ቀናት ውስጥ ተገናኝተው በትግበራው ላይ ውይይት ያደርጋሉ የሚለውን ስምምነት ለመተግበር በእኛ በኩል ያሉት ወታደራዊ አመራሮች ሰኞ ለሚደረገው ውይይት ወደ ናይሮቢ ያቀናሉ።" በማለትም ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

አምባሳደር ሬድዋን በማብራሪያቸው መንግስት ለስምምነቱ ተግባራዊነት አበክሮ እየሰራ መሆኑን ገልፀው እስካሁን ባለው ሂደት ድጋፍ እያደረጉ ላሉ ወዳጅ አገራት ምስጋና ቸረዋል።

መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት አገራት እንዲያግዙ አምባሳደር ሬድዋን ጥሪ አቅርበዋል።

"አጋሮቻችን የሰላም ስምምነቱን እየደገፉት ነው። በርካቶች መልሶ ግንባታውን ለመደገፍ ፍላጎት አላቸው። እንደምታውቁት የትግራይ ክልል በግጭቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል። መንግስት ክልሉን መልሶ ለመገንባት ቁርጠኛ ነው። ይህን ለማድረግ በርካታ ድጋፎች ያስፈልጋሉ በመሆኑም አጋሮቻችን እንዲደግፉን እንጠይቃለን።"

የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላቱ በበኩላቸው የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሚያመጣ እንደሆነ ያላቸውን እምነትና ተስፋ ገልፀዋል።

ስምምነቱ አፍሪካውያን ችግሮቻቸውን በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ምስክርነት የሰጠ መሆኑን በመግለጽ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ጎን ለመቆምና በሚችሉት ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ያላቸውን ዝግጁነትና ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ  ስምምነቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እንደሚያግዝ ገልፀው ጃፓን ለዚህ ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

"የሰላም ስምምነቱ በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት መነሻ ይሆናል።" ያሉ ሲሆን ጃፓን ከአጋሮቿ ጋር በመሆን በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል ገልጸዋል።  

                             

በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሾዛብ አባስ በበኩላቸው ፓኪስታን በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰበት የትግራይ ክልል መልሶ ግንባታ ድጋፍ እንደምታደርግ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ምክትል አምባሳደር ዴቪድ ዳን በበኩላቸው የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፈታት መጀመራቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረው ለዚህ ስኬት እውን መሆን ኃላፊነቱን ለተወጣው የአፍሪካ ህብረት ምስጋና ችረዋል።

አምባሳደር ሬድዋን ለሰላም ስምምነቱ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፆ ላበረከቱ ሁሉ ምስጋና ችረዋል።

በቀጣይ የሰላም ስምምነቱን ወደመሬት በማውረድ ሂደት ሁሉም አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም