የመዲናዋ ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ የታየበት ነው

69
አዲስ አበባ መስከረም 15/2011 በአዲስ አበባ ወጣቶች የተከናወነው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ የታየበት መሆኑ ተነገረ። ከሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የወጣቶች የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመዝጊያ መርሃ ግብር ዛሬ ተካሂዷል። የመዲናዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ወጣቶቹ ያከናወኑት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት "አንዳችን ለሌላችን መኖራችንን የሚያመለክትና ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ የታየበት ተግባር ነው" ብለዋል። "መስጠትና በጎ ተግባር የልባችንና የማንነታችን መገናኛ ነጥብ ነው" ያሉት ምክትል ከንቲባው እያንዳንዳችን የሌላውን ደህንነት ስንጠብቅ ኢትዮጵያዊነት ጎልቶ ይወጣል ነው ያሉት። የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የወጣቶቹን የስራ ተነሳሽነት እንደሚያሳይ ጠቁመው አስተዳደሩ መዲናዋ ለወጣቶች ምቹ እንድትሆን ይሰራል ሲሉ ቃል ገብተዋል። የከተማ አስተዳደሩ እቅድ እንዲሳካ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች "ልታግዙን ይገባል" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። ከከተማዋ ወጣቶች በተጨማሪ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ወጣት ዲያስፖራዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ላደረጉት ተሳትፎም ምክትል ከንቲባው ምስጋና አቅርበዋል። የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጀማሉ ጀምበር ከ850 ሺህ በላይ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስኬታማ እንደነበር ተናግረዋል። በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ 244 የአቅመ ደካሞች ቤቶች መታደሳቸውን እንዲሁም 500 ዩኒት ደም መሰብሰቡን ገልፀዋል። የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት ጥበቡ በቀለ በበኩሉ የዘንድሮው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከታቀደው በላይ ስኬታማ ነበር ብሏል። 'ጥላቻን በመቀነስ ያለንን በማካፈልና ይቅርታን በማብዛት በፍቅር መደመር' የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀመር በተግባር የታየበት ነው ሲል ጠቅሷል። ወጣት በጎ ፈቃደኞች በደም ልገሳ፣ በወጣት ተኮር የጤና አገልግሎት፣ በመንገድ ትራፊክ ደህንነት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በኮምፒውተር ስልጠና፣ በአካባቢ እንክብካቤና በሌሎች ተግባራት ላደረጉት ተሳትፎም ምስጋና አቅርበዋል። በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ግለሰቦች፣ የስፖርት ክለብ ደጋፊዎችና የክፍለ ከተሞች ተወካዮች እውቅናና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል። ለ16ኛ ጊዜ የተካሄደው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት "የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ህብረተሰብን ይገነባል" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከናወነው።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም