በ27ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ አፍሪካ በቂና ተገማች የገንዘብ ካሳ ለማግኘት ትሞግታለች - የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት

142

ጥቅምት 27 ቀን 2015 (ኢዜአ) "አፍሪካ ለመልከ ብዙ ቀውስ የዳረጋትን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም ዓለም በቂና ተገማች ፋይናንስ የሚያቀርበበት ስርዓት እንዲፈጠር መሞገት የ27ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ አንደኛው አጀንዳዋ ነው" ሲል የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት ገለጸ።

27ኛው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባዔ ዛሬ በግብጽ ሻርም አል ሼክ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።።

በርካቶች ጉባኤውን  'የአፍሪካ ጉባዔ' በማለት እየገለጹት ነው።

ተቀማጭነቱን በኡጋንዳ ካምፓላ ያደረገው የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት('አሊያንስ ፎር ፉድ ሶቨርኒቲ ኢን አፍሪካ) የተሰኘው ድርጅትም በጉባኤው የአፍሪካ አጀንዳዎች በጉልህ መስተጋባት እንዳለባቸው ያምናል።

የጥምረቱ አስተባባሪ ዶክተር ሚሊዮን በላይ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በጉባዔው የአየር ንብረት በካይ ጋዞችን ልቀት መቀነስ፣ ተጽዕኖ መቋቋም እና ፋይናንስ አጀንዳዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያነሳሉ።

በተለይም እንደ አፍሪካ የግብርና ብዝሃንትንና ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ ግብርናን ወይም አግሮ ኢኮሎጂ ዕውን ማድረግ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸዋል።

የአፍሪካ ጉዳይ የፖለቲካ መልክ እንዳለው ጠቅሰው፤ ለአብነትም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እንዲሁም በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ሳቢያ አፍሪካ በኢኮኖሚው መስክ  ከፍተኛ ፈተና እንደደረሰባት አመልክተዋል።

በዚህም ለአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት የሕልውና ጉዳይ በመሆኑ፤ ከተፈጥሮ ጋር የተጣጣመ የእርሻ ብዝሃነትና ምርታነማነትን ማሳደግ በጉባኤው ከሚነሱ የአፍሪካ ዐቢይ ትኩረቶች መካከል እንደሚጠቀሱ ነው ዶክተር ሚሊዮን የገለጹት። 

በዚህም ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ብዙ አበርክቶ የሌላት፤ ይልቁንም የከፋ የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስ ገፈት ቀማሽ የሆነችው አፍሪካ፤ በቂና ተገማች የሆነ የገንዘብ ካሳ ክፍያ እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።

በጉባኤው አፍሪካን ለሁለንተናዊ ቀውስ የዳረጋት የአየር ንብረት ለውጥ በተመለከተ ዓለም እንዴት መካስ አለባት? የሚለው ጉዳይ በዋነኛነት ይስተጋባል ብለዋል።

ዛሬ በግብጽ ሻርም አል ሼክ ከተማ የተጀመረው 27ኛው የአየር ንብረት ጉባኤ እስከ ሕዳር 9 ቀን 2015 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ከ190 አገራት በላይ የተወጣጡ ተወካዮች ይሳተፉበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም